የቅድስት ማርያም የእርገት (ሻደይ) በዓል በሰላም እና በፍቅር እንዲከበር ብጹዕ አቡነ በርናባስ አሳሰቡ።

20

ሰቆጣ: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሻደይ በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በደብረ ፀሐይ ወይብላ ቅድስት ማርያም ካቴድራል ተከብሯል። የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ በርናባስ፣ የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሊቀ ህሩያን ኃይሌ ዓለሙ፣ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ፣ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ከፍያለው ደባሽ፣ የደብር አሥተዳዳሪዎች፣ የዕምነቱ ተከታዮች እና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በተገኙበት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የእርገት በዓል ተከብሯል፡፡

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሥራ አሥኪያጅ ሊቀ ህሩያን ኃይሌ ዓለሙ ቅድስት ማርያምን መላዕክት በክንፋቸው እያሸበሸቡ እንዳሳረጓት ኹሉ ዛሬም ደናግል ዘማርያን ከወገባቸው የሻደይ ቄጤማ አዝለው እያሸበሸቡ መዘመራቸው የመላዕክት እና የቅዱሳን ምሳሌ ናቸው ብለዋል።

ሻደይ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ መከበሩ የሚያስመሠግን እና ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡ የቅድስት ማርያምን የእርገት በዓል ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ በርናባስ በዓሉ የሰላም እና የፍቅር በዓል እንዲኾን ተመኝተዋል፡፡ በዓሉን በመከባበር እና በፍቅር ማክበር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በበዓሉም የሃይማኖት አባቶች ወረብ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን መዝሙር፣ ሃይማኖታዊ ይዘቱን የጠበቀ ትምህርት እና የሻደይ በዓልን የተመለከተ ትምህርት ቀርቧል። በቀጣይም በብሔረሰብ አሥተዳደር ደረጃ በዓሉ እንደሚከበር ነው የተገለጸው፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሀ ግብርን በማስመልከት ያስተላለፉት መልእክት፦
Next articleየአዲስ አበባ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ በተለያዩ ደረጃዎች እና የሙያ ዘርፎች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።