“ባለሃብቶችን ለመሳብ ምቹ ኹኔታዎች እንፈጥራለን” የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ

13

ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አልሚ ባለሃብቶችን ለመሳብ የክልሉን ጸጋዎች ማስተዋወቅ እና ምቹ ኹኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባ የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አሳስቧል። ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸዉን ይዘዉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በማዉጣት ወደ ሥራ መግባት እንዲችሉ በክልሉ ያሉትን ጸጋዎች የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል። በዚህም ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማዉጣት ፍላጎት ያሳያሉ፡፡

አንድ ባለሃብት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማግኘት ይዞት የሚመጣዉ የፕሮጀክት አማራጭ ከግምት ዉስጥ ይገባል፤ ሲሉ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ንጉሴ አማረ ተናግረዋል፡፡ ኀላፊው እንዳሉት ባለሀብቶች በክልሉ ሊፈጥር የሚችለዉን የሥራ እድል እና በክልሉ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የሚያበረክተዉን አስተዋጽኦ ታሳቢ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ይሰጠዋል ነው ያሉት፡፡

እንደየአካባቢዎቹ የመልማት እድልና የባለሀብቶቹ የካፒታል አቅምም ፈቃድ ለመስጠት ሌላዉ መስፈርት እንደኾነ ነዉ የተናገሩ፡፡ የመነሻ የፋይናንስ አቅም የሚወሰነዉ በሚያቀርቡት የፕሮጀክቶች ባህሪና እንደየአካባቢዉ የመልማት አቅም እንደኾነም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በጣም የተሻለ የኢንቨስትመንት ፍስሰት ባለባቸዉ አካባቢዎች የተሻለ የኢንቨስትመንት ዉድድር ስለሚኖር የተሻለ የሥራ እድል የሚፈጥር፣ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ያለዉ መኾኑ ታይቶ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲያለማ እንደሚደረግም ተናግረዋል ፡፡

አንድ ባለሀብት በመንግሥት የተዘጋጀዉን የማበረታቻ እድል የማግኘት መብት አለዉ ብለዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለሀብቱ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ ወደ ሥራ የመግባት ፣ የሥራ እድል የመፍጠር፣ በክልሉ ባለዉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አወንታዊ ሚና የመፍጠር ይኖርበታል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአቅርቦት እጥረት ምክንያት ለመጪው በዓል በሚውሉ ምርቶች ላይ የዋጋ መናር እንዳይፈጠር በቂ ዝግጅት መደረጉን ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አስታወቀ።
Next articleየክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው።