
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ለዘመናት የቆየውን ታሪካዊ ግንኙነት የሚመጥን የሩሲያ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ተሳትፎ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና እንዲኖር በትኩረት እንደሚሠራ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ.ር ) ገለጹ፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህን የገለጹት በሩሲያ ሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ሮዛ የሩቅነህ ጋር በበይነ መረብ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡ ዶክተር ፍስሃ ይታገሱ በበይነ መረብ ውይይቱ የሩሲያ ባለሃብቶች በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በአውቶሞቢል እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል። ሩሲያ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም ከኤምባሲው ጋር በትብብር ይሠራልም ብለዋል፡፡
በሞስኮ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ምክትል አምባሳደር ሮዛ የሩቅነህ በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ያላቸው ትብብር ታሪካዊ ነው ብለዋል። አሁን ላይ ሩሲያውያን ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መኾኑን የገለጹት ምክትል አምባሳደሯ ለፍላጎቱ ተግባራዊነት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ በቀጣይ በሩሲያ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ እና የኢንቨስትምንት ፎረሞች በመሳተፍ ፍላጎት ካሳዩ ኢንቨስተሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ የሩሲያ ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሠራ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
