
ሰቆጣ: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኹሉም አካባቢዎች እና በብሔረሰብ አሥተዳደር ደረጃ የሚከበረውን የሻደይ በዓልን በማስመልከት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሻደይ ለሴቶች የነጻነታቸው፣ ለማኅበረሰቡ የመጠያየቂያ፣ ለወጣቱ የመዋቢያ ቀን ነው ያሉት አቶ ኃይሉ ይህ በዓል በዋግ ኽምራዎች ዘንድ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው እንደኾነም ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር በማዕከል ደረጃ ማክበር አለመቻሉን ያስታወሱት አቶ ኃይሉ በዚህ ዓመት ግን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያለውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም ” ሻደይ ባሕላችን ለዘላቂ ሰላማችን እና ለአንድነታችን” በሚል መሪ መልዕክት በሰቆጣ ከተማ እና በመላው ዋግ ኽምራ በድምቀት ይከበራል ብለዋል።
የሰሃላ ሰየምትን ሕዝብ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚያገናኘው የተከዜ ድልድይ ለአገልግሎት ክፍት በኾነበት፣ ዋግ ኽምራ የተለያዩ የልማት መሠረተ ልማቶች ተጠቃሚ እየኾነች ባለችበት፣ የሌተናል ጄኔራል ኃይሉ ከበደ መታሰቢያ ሙዚየም ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ በተቀመጠበት ዓመት የሻደይ በዓል መከበሩ ልዩ ድምቀት ይሰጠዋል ነው ያሉት።
የሻደይ በዓል ሲከበር በፍጹም ሰላም እና መተሳሰብ ሊኾን እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ዋና አሥተዳዳሪው በአካባቢው ያለውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል የታጠቁ ኀይሎችን በመምከር እና በመሸምገል ወደ ሰላም እንዲመጡ ማድረግ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሰላም ካውንስሉ አባላት ይጠበቃል፤ መንግሥትም ለሰላም በሩ ክፍት ነው ብለዋል።
“በ2016 ዓ.ም የሚከበረው የሻደይ በዓል የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት በዓል እንዲኾንላችሁ እመኛለሁ ” ሲሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
