መሪዎች የመንግሥት የሥራ አቅጣጫዎችን አውቀው እየሠሩ ስለመኾኑ ማረጋገጫ የተወሰደበት ውይይት ማድረጋቸውን ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ገለጹ።

26

ደሴ: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በክልሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር የተመራ የክልሉ ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች እና የምክር ቤት አባላትን ያካተተ ልዑክ በቃሉ ወረዳ እና ሀርቡ ከተማ የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ምልከታ እና ውይይት አካሂዷል። የሥራ ኀላፊዎቹ ከጉብኝቱ ባሻገር ከተለያዩ የቀበሌ መሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ውይይቱ በልማት እና በሰላም ጉዳይ ላይ ያተኮረ መኾኑን ነው የገለጹት።

መሪዎች የመንግሥት የሥራ አቅጣጫዎችን አውቀው እየሠሩ ስለመኾኑ እና የሕዝቡ ተጠቃሚነት ምን ያክል ተረጋግጧል የሚሉ ጉዳዮች ታይተው ማረጋገጫ የተወሰደበት ውይይት ስለማድረጋቸው ነው ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ያስገነዘቡት።

በውይይቱ ወቅት የቀበሌ ባለሙያ እና መሪዎች እያከናወኗቸው ያሉ ሥራዎችን አብራርተዋል። ከሰላም እና ፀጥታ፣ ከግብርና ሥራ እና ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን የቀበሌ መሪዎቹ አንስተዋል።

ነዋሪዎቹም ቢፈቱ ያሏቸውን የንፁህ መጠጥ ውኃ እና የጤና መድኅን አገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ የሆስፒታል ግንባታ ጥያቄ፣ ከመልካም አሥተዳደር አኳያ ማኅበረሰቡን ለማርካት ያለው አሠራር ቢፈተሽ ሲሉ አንስተዋል። የማዳበሪያ እጥረት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ይበልጥ እንዲሠራም ጠይቀዋል።

በውይይቱ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር )፣ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን፣ የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው ( ዶ.ር)፣ የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኛው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንዲሁም የዞን እና የወረዳ መሪዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- ሙሐመድ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ317 ሺህ ሄከታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next articleየሻደይ በዓል ሲከበር በፍጹም ሰላም እና መተሳሰብ ሊኾን እንደሚገባ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።