ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ317 ሺህ ሄከታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

33

አዲስ አበባ: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ወቅታዊ ጉዳዩችን በተመለከተ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ መግለጫ ሰጥቷል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የአረንጓዴ አሻራ ልማትን እንደትልቅ አቅም እየተጠቀመችበት ነው ብለዋል በመግለጫቸው።

ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ከማለዳው 12:00 ሰዓት እስከ ምሽት 12:00 ሰዓት በሚካሄደው በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር 317 ሺህ 521 ሄክታር መሬት ለተከላ ዝግጁ መደረጉን ገልጸዋል።

ባለፋት አምስት ዓመታት በተካሄዱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች 32 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ዘንድሮ እንደ ሀገር ከሚተከለው 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ጋር ተዳምሮ 40 ቢሊዮን ለመድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር 50 ቢሊዮን ችግኞችን እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ ለመትከል የሚያስችል አቅም መፈጠሩንም ዶክተር ግርማ አመንቴ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በ2030 የደን ሽፋኗን 30 በመቶ ለማድረስ እየሠራች መኾኑንም ሚኒስትሩ አመላክተዋል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ እንደ ሀገር ሚሊዮኖች በሚሳተፉበት የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አዋቂዎች 20 እና ከዚያ በላይ ሕጻናት ደግሞ 10 እና ከዚያ በላይ እንዲተክሉ አደራ ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአረብ ኢምሬት ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮዲንግ የዲጂታል ሥልጠና ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ሁሉ በቀላል አማራጭ ስልኮቻቸውን በመጠቀም ዲጂታል የኦንላይን ሥልጠናዎችን በመውሰድ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበተጠናቀቀው በጀት ዓመት 20 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጽያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
Next articleመሪዎች የመንግሥት የሥራ አቅጣጫዎችን አውቀው እየሠሩ ስለመኾኑ ማረጋገጫ የተወሰደበት ውይይት ማድረጋቸውን ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ገለጹ።