
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ እና የሪሾን ለፂዮን ከተማ የእህትማማችነት ግንኙነት ለመመሠረት የተስማሙት በ1998 ዓ.ም ነበር፡፡
ይህም ግንኙነት በልዩ ልዩ ምክንያት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ ይህን ግንኙነት ለማጠናከር በጎንደር ከተማ ከንቲባ የሚመራ ልዑክ ከነሐሴ አምስት ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሀገረ እስራኤል ተጉዞ ከሪሾን ለፂዮን ከተማ ተወካዮች ጋር ፍሬያማ ውይይቶች እና የልምድ ልውውጦችን አካሂዷል፡፡
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይን ጨምሮ ከከተማ አሥተዳደሩ ከተለያዩ ሴክተሮች የተውጣጣ የልዑካን ቡድን ከተማዋን ጎብኝቷል፡፡
የልዑካን ቡድኑን የመሩት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ጉብኝቱን አስመልክቶ እንደገለጹት የልዑካን ቡድኑ የጉብኝት ቆይታቸው ውጤታማ እና ፍሬያማ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የጉብኝቱ ዓላማ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የነበረውን የጎንደር ከተማ እና የሪሾን ለፂዮን ከተማ የእህትማማችነት ግንኙነት እንደገና ለማጠናከር ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
“ዘመኑ የከተሞች ነው” ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የከተማዋን አቅሞች በመለየት፣ ዕድሎችን በመጠቀም እና ተግዳሮቶችን ከመቀነስ ጎን ለጎን በዓለም ላይ ካሉ እና ከሀገሪቱ ከተሞች ልምድ መቅሰም ብሎም በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በሀገረ እስራኤል በርካታ በጎንደር እና አካባቢው የነበሩ ቤተ-እስራኤላዊያን ለሁለትዮሽ ግንኙነቱ ውጤታማነት አቅም አድርጎ መጠቀም የሚያስችል ዕድል መኖሩ ጉብኝቱን ልዩ እንዳደረገው ገልጸዋል።
ሁለቱ እህትማማች ከተሞች በቱሪዝም፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በወጣቶች፣ በከተማ መልሶ ማልማት እና በዲጅታላይዜሽን ዘርፎች በጋራ ለመሥራት መግባባታቸውን ተናግረዋል፡፡
በጎንደር እና አካባቢዋ ይኖሩ የነበሩ ቤተ-እስራኤላዊያን በጎንደር ከተማ ሙዚየም እንዲገነቡ እና የቱሪዝም ትስስሩን የበለጠ ለማጠናከር መግባባት ላይ መድረሳቸውን ከጎንደር ከተማ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!