
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዘንድሮው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ነሐሴ 17 እንደሚካሄድ እና በዚህም 600 ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መግለጻቸው ይታወሳል።
በዕለቱ አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊዎች ከ10 በላይ ችግኝ በመትከል ለነገ ሀገር ተረካቢዎች የምትመች ሀገር ለማስረከብ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ኅላፊነታችንን እንወጣ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ይህን ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የኾኑ ተፎካካሪዎች በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ሁሉም የማኀበረሰብ አባላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል አሕመድ ሰይድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ አጀንዳዎቻችንን በመለየት ለከተማችን ነዋሪዎች ጥቅም እና ዕድገት እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
በተለይም “በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የተፎካካሪ ፓርቲዎች ያለምንም ልዩነት በጋራ እየተሳተፉ” ነው ብለዋል።
በመጪው አርብ በሚከናወነው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን በመጠቆም በዕለቱ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትም ኾኑ የመዲናዋ ነዋሪዎች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች ሳይገደቡን በሀገር ጉዳይ አንድነታችንን የምናሳይበት ሊኾን ይገባል ብለዋል።
በዚህም በሀገር ጉዳይ አንድነታችንን አጠናክረን የጋራ አሻራችንን በማኖር ለትውልድ ምቹ ሀገር ለማውረስ በጋራ ተቀራርበን መሥራት አለብን ነው ያሉት።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የአሥተዳደር አካላት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!