“ድርድርና ውይይት የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፍ በመኾኑ ገለልተኛ ኾኖ የተቋቋመውን የሰላም ካውንስል ሕዝቡ ሊደግፍ ይገባል” አቶ ደሳለኝ ጣሰው

15

ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን ላይ በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች የትራንስፖርት አግልግሎት በመዝጋት የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ ቀውስ ለማባባስ የታጠቁ ኀይሎች እየፈጸሙ መኾኑን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ገልጸዋል።

መንግሥት የሰጠውን የድርድርና የውይይት ዕድል ወደኃላ በመተው የታጠቁ ቡድኖች ጥፋት እየፈጸሙ መኾኑንም ነው የተናገሩት።

የታጠቁ ቡድኖች የተቋቋመው የሰላም ካውንስል እያደረገ ያለውን የሰላም ጥሪ ወድ ጎን በመተው ችግሩን በማባባስ ላይ እንደሚገኙም ነው አቶ ደሳለኝ የገለጹት።

መንግሥት ያደረገውን የሰላም ጥሪ መልካም እድል ከመጠቀም ይልቅ መንግሥትን እንደተዳከመ በመቁጠር የተቋቋመውን የሰላም ካውንስል የማገትና የማሽማቀቅ ሥራ እያከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

ድርድርና ዉይይት የሁሉም ነገረ መፍቻ ቁልፍ መኾኑን ገልጸው ገለልተኛ ኾኖ የተቋቋመዉን የሰላም ካውንስል ሕዝቡ ሊደግፍ ይገባል ነው ያሉት። ካውንስሉም የጀመረዉን የውይይት ሥራ አጠናክሮ መሥራት እንደሚገባዉ አሳስበዋል፡፡

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ጠንካራ የተደራጀ የሕግ ማስከበር ሥራ የክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በትኩረት እንደሚሠራም አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳደሪ ወርቁ ኀይለማሪያም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ገለልተኛ ኾኖ የተቋቋመዉ የሰላም ካውንስል ችግሩን ለመፍታት ጥረት ሲያደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ክልሉ ያጋጠመውን ችግር በሰላማዊ ውይይት ከመፍታት ይልቅ መንገድ መዝጋትና ሌሎች ጥፋቶችን ሲፈጽሙ ይስተዋላል ነው ያሉት አቶ ወርቁ። ጥፋቱን ለማስቆም ሲባልም ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የ102ኛ ኮር ዋና አዛዥና የጎንደርና የማዕከላዊ ጎንር ዞን ኮማንድፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴን ጀኔራል መካሽ ጀንበሬ ኅብረተሰቡ ልማት እንዳያለማ የታጠቁ ኀይሎች እያሸማቀቁት ነዉ ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ልማት የጠማው በመኾኑ በአጭር ጊዜ ሰላምን ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ ጀኔራሉ መግለጻቸውን ከከተማው ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ሸዋ ዞን ስምንት ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከሰተ፡፡
Next articleተፎካካሪ ፓርቲዎች በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ሁሉም ማኀበረሰብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ።