
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ስምንት ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት መከሰቱን የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበባው መሰለ በክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ እና የመሬት መንሸራተት ሊያጋጥም እንደሚችል ማስጠንቀቂያዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አሥር ቀናት ውስጥ በዞኑ አራት ወረዳዎች ላይ የጎርፍ አደጋ መከሰቱን አንስተዋል፡፡ ቀወት፣ መንዝ ቀያ፣ ኤፍራታና ግድም እና አንጾኪያ ወረዳዎች ደግሞ አደጋው የተከሰተባቸው ናቸው ብለዋል፡፡ የጎርፍ አደጋ በተከሰተባቸው ወረዳዎች በ113 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ወድሟል ነው ያሉት፡፡ ሰባት የመኖሪያ ቤቶች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ጠፍተዋል ብለዋል፡፡ በእንስሳት እና በሌሎች ሰብሎችም ጉዳት እንደደረሰ ነው የተናገሩት፡፡
በተፈጠረው የጎርፍ አደጋ 647 የቤተሰብ ኀላፊዎች የጉዳቱ ሰለባ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላም የጎርፍ አደጋ ሊከሰትባቸው የሚችሉ አካባቢዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም አስገንዝበዋል፡፡ ጥንቃቄ ካልተደረገ የጎርፍ ሰለባ ሊኾኑ የሚችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ጥንቃቄ እንዲደረግ በተቻለ መጠን ግንዛቤ እየተፈጠረ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
በዞኑ ስምንት ወረዳዎች ላይ የመሬት መንሸራተት መከሰቱንም አስታውቀዋል፡፡ በተፈጠረው የመሬት መንሸራተት 264 ነጥብ 12 ሄክታር ማሳያ ላይ የተዘራ ሰብል እና ቋሚ አትክል ተጎድቷል ነው ያሉት፡፡ አምስት ሄክታር የግጦሽ መሬት ጉዳት እንደደረሰበትም ተናግረዋል፡፡ 166 መኖሪያ ቤቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የውኃ ተቋማት እና መንገድ ላይም ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት፡፡
በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ አደጋው ባልተጠበቀ ሁኔታ የሚከሰት በመኾኑ ምላሽ ለመስጠት አስቸጋሪ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩም በፍጥነት ድጋፍ ለማድረግ አስቸጋሪ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
ማኅበረሰቡ ለቅድመ ጥንቃቄ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መኾኑ ጉዳት እንዳያስከትል ያሰጋል ነው ያሉት፡፡ ማኅበረሰቡ ሳይንሳዊ የኾኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መመሪያዎችን መተግበር እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ ለተጎጂ ወገኖች በተቻለ መጠን ድጋፍ ለማድረግ ርብርብ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!