
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ጤና መምሪያ የ2016 የሥራ አፈጻጸም እና የ2017 የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ እንዳሉት የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ በ2016 በጀት ዓመት በችግር ውስጥ ኾኖም በከተማዋ የጤና አገልግሎት ሳያቋርጥ ኅብረተሰቡን ማገልገል መቻሉ አንዱ የጥንካሬው ምልከት ነው፡፡
ቢሮ ኀላፊው ጤና መምሪያው ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከግብዓት አቅርቦት እና ከጤና ሙያተኞች ሥነ ምግባር ጋር ተያይዞ ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸውን የቅሬታ ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ በመረዳት የአሠራር ሥርዓት ዘርግቶ መሥራት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ የመልካም አሥተዳደር ችግሮቹን በተደራጀ አግባብ በመፍታት የመንግሥት የጤና ተቋማት ከግሉ የጤና ተቋማት ጋር የሚኖራቸውን የአገልግሎት ቁርኝት በማሥተሳሰር የኅብረተሰቡን የሕክምና እርካታ መፍጠር እንደሚገባም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
“የግል እና የመንግሥት የጤና ተቋማት ደረጃቸውን ጠብቀው በመሥራት ለሕሙማን የተመቹ፣ ጽዱ እና ውብ ብሎም ፈውስ የሚገኝባቸው መኾን ይኖርባቸዋል” ነው ያሉት አቶ አብዱልከሪም፡፡ በጤናው ዘርፍ ማኅበረሰቡ የሚነሳቸው ጥያቄዎችን ለመፍታት የግል እና የመንግሥት የጤና ተቋማት ደረጃቸውን ጠብቀው መሥራታቸውን የበለጠ መቆጣጠር እንደሚገባ የጠቆሙት ቢሮ ኀላፊው በዚህ መልኩ ከተሠራም የተሟላ የመድኃኒት እና የሕክምና መሳሪያዎች አቅርቦትም ይኖራል ብለዋል፡፡ቢሮ ኀላፊው በባሕር ዳር ከተማ የተጀመረውን የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት በቀጣይ ማስፋፋት እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ በ2016 በጀት ዓመት የከተማዋ ጤና መምሪያ ችግሮችን በመቋቋም በእናቶች እና ሕጻናት ጤና ላይ አበረታች ሥራ መሥራቱን አወድሰዋል፤ በተለይ ደግሞ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅንን ተጠቃሚዎች ከ78 በመቶ በላይ ማድረሱ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ ጤና መምሪያ ኀላፊ ሲስተር ዓለም አሰፋ ክልሉ የገጠመው ወቅታዊ ችግር ሳይገድባቸው ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎት መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኀላፊዋ የእናቶች ሞትን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብረው በመሥራታቸው 25 ሺህ ለሚጠጉ እናቶች የቅድመ እና የድህረ ወሊድ አገልግሎት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናትም የኩፍኝ መከላከያ ክትባት በመስጠት ይደርስ የነበረውን ሞት መቀነሳቸውን ነው ያብራሩት፡፡
በከተማዋ ውስጥ ይበልጥ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን ጠቁመው በአዲስ በኤች አይቪ ቫይረስ የተያዙትን በመለየትም መድኃኒት እንዲጀምሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ የወባ በሽታን ለመከላከል የተሠራው ሥራ ጠንካራ ቢኾንም ሥርጭቱ ከፍተኛ ስለኾነ በማኅበረሰብ ደረጃ ወባን የመከላከል እና የመቆጣጠር ተግባርን ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ሲስተር ዓለም የጠቆሙት፡፡
የጤና አገልግሎት ወጪን ለመቀነስ ከ47 ሺህ በላይ አባዎራዎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፤ ከዚህም ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ መሠብሠቡን የመምሪያ ኀላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!