“ወልድያን ሊቀይሩ የሚችሉ የልማት ሥራዎች በጥሩ ኹኔታ ቀጥለዋል” የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራር

25

ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰሞኑ በአማራ ክልል ታላላቅ ከተሞች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲኖር፣ መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዲገደቡ የሚወጡ መረጃዎች ነበሩ፡፡ በሚወጡ መረጃዎች ምክንያት ነዋሪዎች ተደናግጠዋል፡፡ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲኖር መረጃዎች ከወጡባቸው ከተሞች መካከል ወልድያ ከተማ አሥተዳደር አንደኛዋ ናት፡፡

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራር በከተማዋ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ነው፣ የኑሮ ማረጋጋት ሥራዎችን በትኩረት እየሠራን ነው፣ መንግሥታዊ ተልዕኮዎችንም እየፈጸምን ነው ብለዋል፡፡
በከተማዋ ዞናዊ ውይይቶች እና ምክክሮች ሲደረጉባት መሰንበቷንና ሲያጠናቅቁ በሰላም መሸኘታቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የታጠቀው ቡድን ወደልድያ ከተማ ከሰሞኑ ብቻ ሳይኾን ከዚያ በፊትም፣ ዛሬም ቢችሉ በርካታ ድርጊት ለመፈጸም ፍላጎት አለው ነው ያሉት፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የጸጥታ ተቋማት በሚሠሩት ሥራ ግን ይሄን ማድረግ አይቻልም ብለዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ኑሯቸውን ለማቃናት ሥራ ላይ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንደሚወሩ የሐሰት መረጃዎች ሳይኾን ወልድያ ልማቷን እያከናወነችና ሥራዋን እየሠራች ነው ብለዋል፡፡ ወደ ከተማ ሰርጎ በመግባት የማፈንዳት፣ የትራንስፖርት መስጫ ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ለማወክ የተደረጉ ሙከራዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ተውን ሥራችንን ነው የምንሠራው በማለት አገልግሎት ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡ በከተማዋ ያልተገባ ነገር ለመፍጠር የሞከሩ አካላት አሉ አልተሳካላቸውም፣ ሊሳካላቸውም አይችልም ብለዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች በሚናፈሱ ሐሰተኛ መረጃዎች እንዳይረበሹ ከተማ አሥተዳደሩ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ባጃቾች ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከረውን አካል በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ሕዝብ ሠርቶ እንዳይበላ፣ ኑሮ እንዳይመቸው ለማድረግ መሥራት ተገቢ አለመኾኑንም አመላክተዋል፡፡ በሐሰተኛ መረጃዎች እና ወሬዎች የሚረበሽ ሕዝብ አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ ሰላም በጥሩ ኹኔታ ላይ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የወልድያ ሕዝብ ሠርቶ ለመለወጥ ሌት ተቀን የሚለፋ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የወልድያ ሕዝብ ግጭት እና ጦርነት የሰለቸው መኾኑን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ራሱን በማደራጀት አካባቢውን እየጠበቀ ነው፣ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመኾን በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ሕዝቡ እያደረገው ባለው መልካም ሥራ ጥቃት ለመፈጸም ሰርገው የሚገቡ ኃይሎች እየተያዙ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ወቅታዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የዋጋ ንረት እንዳይኖር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የዋጋ ንረት የተስተዋለባቸውን ምርቶችን የማረጋጋት ሥራ ተሠርቷልም ብለዋል፡፡

ወልድያን ሊቀይሩ የሚችሉ የልማት ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ ቀጥለዋል ነው ያሉት፡፡ በከተማዋ የሌማት ቱሩፋት፣ የችግኝ ተከላ ንቅናቄ ሥራዎችም መቀጠላቸውን ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ የቁጭት እቅድ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የአሸንድዬ እና የሶለል በዓላት እንዲከበሩ በሚመለከታቸው አካላት ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር እየተወያዩ የልማት ሥራዎችን ማስቀጣለቸውንም አንስተዋል፡፡ ሕዝቡ ለሰላም እየሠራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡

ወልድያን ከንግድ ማስተጓጎል፣ ከተማዋን መጉዳት የአማራን ሕዝብ መጥቀም አይደለም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ወደኋላ የሚመልሱ አካሄዶችን መቃወም እና የተጀመሩ የሰላም እና የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ልጇን በግፍ ለተነጠቀቸው የሕጻን ሄቨን እናት የመኖሪያ ቤት አበረከተ።
Next articleከጦርነት መውጫችን መቼ ነው ?