
ጎንደር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ትምህርት ለትውልድ የ2017 ዓ.ም የንቅናቄ መድረክን አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የመሬት መምሪያ ኀላፊ አላምረው አበራ በዞኑ 1 ሺህ 79 ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ 300 በላይ ትምህርት ቤቶች በፀጥታ ችግር ምክንያት ተዘግተው መቆየታቸውን አንስተዋል።
በዚህም 150 ሺህ ያክል ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል። ያለፈው ዓመት ችግር ሳይደገም ሁሉም ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ የፀጥታ ተግባሩ ላይ ይሠራል ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምርያ ኀላፊ ክንዱ ዘውዱ እንዳሉት በዞኑ ከሚገኙ 1ኛ ደረጃ ትምርት ቤቶች ውስጥ 80 በመቶ ያክሉ ከደረጃ በታች ናቸው። በዞኑ ካሉ 52 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 94 በመቶ ያክሉ ከደረጃ በታች ስለመኾናቸውም አንስተዋል።
በመጭው የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ 40 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከመጭው ነሐሴ 20 እስከ መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም በሁሉም ትምህርት ቤቶች ምዝገባ ይካሄዳል ያሉት አቶ ክንዱ በዞኑ ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዷል ብለዋል።
በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀለፊ ተመልከት አዲስ እና የጭልጋ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘሪሁን ንጉሴ ለ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ቅድመ ዝግጅት ሥራ የክረምት ማጠናከርያ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል። ለ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ቅደመ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዘውዱ ማለደ የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ለማሳደግ የምገባ መርሐ ግብር ላይ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ባለሃብቶች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና የሥራ ኀላፊዎች በንቅናቄ ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከመጭው መስከረም 7/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንደሚጀመርም በመድረኩ ተነስቷል።
ዘጋቢ፡- አዲስ ዓለማየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!