ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲኾን መከበር ያለባቸው የሥነ-ምግባር መርሆች፦

60

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች እና ባለድርሻ አካላት በሀገራቸው ጉዳይ ላይ መክረው እና ዘክረው የማኀበራዊ ውሎቻቸውን የሚያድሱበት ሂደት መኾኑ የሚታወቅ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማኀበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው በምክክር ሂደቱ ላይ የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎችን እና ባለድርሻ አካላትን በመወከል ተሳታፊ የሚኾኑ ተወካዮች በተወሰኑ የጋራ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አመለካከቶችን እና ፍላጎቶችን ሊያንጸባርቁ እንደሚችሉ ቢገመትም ለሚከተሉት የሥነ-ምግባር መርሆዎች ተገዢ መኾናቸው ሂደቱን ሰላማዊ ያደርገዋል፡፡

1. በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ አካላት አንዳቸው ሌላውን በማክበር፤ ርህራሄን በማሳየት አንደኛው ወገን ስለሌላኛው ወገን ለማወቅ ጥረት ማድረግ፤ የተለያዩ አመለካከቶችን ለመረዳት ፈቃደኛ መኾን፤

2. በሀገራዊ ምክከሩ ላይ የሚሳተፉ አካላት አንዳቸው ሌላኛቸውን ወገን ከማንኳሰስ እና የሥነ-ልቦና የበላይነትን ለመያዝ ከመሞከር ይልቅ በሰው ልጅ እኩልነት በጥብቅ ማመን፤

3. በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ተሳታፊ የሚኾኑ ባለድርሻ አካላትን፣ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን ስብዕናቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ ተቃውሞ እና ትችትን ከመሰንዘር በመቆጠብ በሀሳብ እና በርዕዮተ-ዓለም ደረጃ ሀሳብ ማቅረብ፤

4. በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት የማኀበረሰቡን እሴቶች ባከበረ መልኩ የምክክሩን ሂደት ማስኬድ፤

5. በሂደቱ ላይ ተሳታፊ የሚኾኑ ባለድርሻ አካላት የምክክር ሂደቶቹ ውስንነቶች እንሚኖራቸው በመረዳት ከግልፍተኝነት በፀዳ መልኩ ሌሎች ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ መሣሪያዎችን የሂደቱ አጋዥ አድርገው ለመጠቀም ፈቃደኛ መኾን የሚሉት ናቸው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍትሕ ሥርዓቱ ራሱን እንዲፈትሽ ተጠየቀ።
Next article“ከመጭው መስከረም 7/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ትምህርት ይጀመራል” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን