የፍትሕ ሥርዓቱ ራሱን እንዲፈትሽ ተጠየቀ።

44

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በህጻን ሔቨን ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ወንጀል የሃይማኖት አባቶች አውግዘዋል።

በፈለገ ግዮን አንድነት ገዳም የፔዳ ተክለሃይማኖት አገልጋይ አባ እንድርያስ አምባቸው በሕጻን ሔቨን ላይ የተፈጸመው ድርጊት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮት በእጅጉ ያፈነገጠ እና እኩይ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በሕጻኗ እና በቤተሰቦቿ ላይ ለደረሰው አደጋ ተጠያቂው የድርጊቱ ፈጻሚ ብቻ ሳይኾን እኛ የሃይማኖት አገልጋዮች እና አስተማሪዎችም ጭምር ነን፡፡ “ግብረ ገብን እና ሌሎች ማኅበራዊ እሴቶቻችንን በተገቢው መልኩ ለማኅበረሰቡ ሳናስተምር ጣታችንን በአጥፊዎች ላይ ብቻ መቀሰር የለብንም” ብለዋል፡፡

አባ እንድርያስ የሃይማኖት አባቶች እና የሃይማኖት አገልጋዮች የመንፈስ ልጆቻችን ‘ኑ አባት ኹኑን’ ሲሉን ብቻ ሳይኾን እኛ ወደ እነሱ ሄደን አባት መኾንም ይገባናል ነው ያሉት፡፡

በሕጻን ሔቨን ዙሪያ ማኅበረሰቡ እያነሳ ያለው የፍትሕ ጥያቄ ተገቢነት ያለው ነው ብለዋል፡፡ “በኛ ሀገር ደም የመመላለስ መጥፎ ልማድ የመጣው አጥፊዎች በፍትሕ አደባባይ በአግባቡ እየተቀጡ ባለመኾናቸው ነው ብለዋል፡፡ አጥፊዎች ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ የኾነ ቅጣት ማግኘት አለባቸው፤ ቅጣቱ ሌሎችንም ከጥፋት የሚያርቅ እና የሚያስተምር መኾንም ይገባዋል ብለዋል፡፡

በሕጻን ሔቨን ላይ የተፈጸመው በደል ከሰዋዊነት ባህርይ ያፈነገጠ ነው፤ የዚህ ዓይነቱን አስጸያፊ ድርጊት እንስሳትም አይፈጽሙትም፤ የዚህ ድርጊት ፈጻሚ ምድር ላይ ባለ በየትኛውም ቅጣት ቢቀጣ ከጥፋቱ ጋር ተመጣጣኝ ሊኾን አይችልም ነው ያሉት፡፡

አሁን ላይ ለተጎጂዋ ቤተሰቦች መጽናናትን ከመመኘት ባለፈ የሀገራችን የፍትሕ ሥርዓት በአግባቡ ሊቃኝ ይገባዋል ብለዋል አባ እንድርያስ፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የየትኛውም ሃይማኖት መሪዎች ለተከታዮቻቸው መልካም ሥነ ምግባርን ለማውረስ እና መልካም እሴቶችን ለማስቀጠል ጠንክሮ መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡

ሰዎች በሰዎች ላይ የሚፈጽሙትን ዘግናኝ በደል ታስሮ በመፈታት ደረጃ አቅልለው ስለሚያዩት ወንጀልን ለማቆም አስቸጋሪ እየኾነ መጥቷል ይላሉ የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ ኡስታዝ አቡበከር፡፡

ይህ በመኾኑም ጨካኞችን በተገቢው የሚያርም ሕግ መኖር አለበት፡፡ የሰው ልጅ እንኳንስ ለመድፈር እና ለማነቅ ቀርቶ ለማየት የሚያሳሱ ሕጻናትን ደፍሮ የሚገድል ከኾነ ምን ዓይነት ሕግ ሊበጅለት ይገባል? በእነዚህ ዓይነት ጨካኝ ሰዎች ላይስ አስተማሪ ቅጣት ካልተጣለ የሕግ ትርጉሙ ምንድነው? ፍትሕስ ምንድነው? ሲሉ ይጠይቃሉ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፡፡

“በቁርዓን አስተምህሮት ውስጥ አንዲት ህያው ነፍስን ያጠፋ ሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደፈጸመ ይቆጠራል“ ብለዋል ኡስታዙ፡፡

“ፈጣሪ የሰጠንን ነፍስ ለመንጠቅ ከእሱ ውጪ ሥልጣን የተሰጠው አካል የለም“ ያሉት ኡስታዝ አቡበከር ብዙ አረመኔ ሰዎች ግን ይሄንን ሕግ በመተላለፍ በርካታ አረመኔያዊ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ እያየን ነው ብለዋል፡፡

ሕጻን ልጁ ተገዳ ተደፍራበት፣ በዚያም ላይ ታንቃ የተገደለችበት ወላጅ በድርጊቱ ፈጻሚ ላይ እንኳንስ ለዓመታት መታሰር ይቅርና ዕድሜ ልክስ ቢፈረድበት እንዴት በፍርዱ ሊረኩ ይችላሉ? ሲሉ መምህሩ ይጠይቃሉ፡፡

የሰው ልጆች ለሚፈጸምባቸው ዘግናኝ ድርጊቶች አስተማሪ ፍትሕ የማይሰጠው እና ሌሎች አጥፊዎችን የሚያበረታታው የሀገራችን የፍትሕ ሥርዓት ራሱን ሊፈትሽ ይገባዋል፤ የሰዎች የመኖር ዋስትናም በተገቢው መንገድ መረጋገጥ እንዳለበት ለመንግሥት ማሳሰብ እወዳለሁ ሲሉ ነው ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ በማኅበራዊ የትሥሥር ገጻቸው ስለ ሕጻን ሔቨን መልዕክታቸውን ያጋሩት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በራስ አቅም ለመልማት ግብርን በወቅቱ መክፈል ባሕል ሊኾን ይገባል” ግብር ከፋይ
Next articleሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲኾን መከበር ያለባቸው የሥነ-ምግባር መርሆች፦