“በራስ አቅም ለመልማት ግብርን በወቅቱ መክፈል ባሕል ሊኾን ይገባል” ግብር ከፋይ

28

ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ግብር መንግሥት በሕግ እና ደንብ ላይ ተመስርቶ ከሕዝብ እና ከድርጅቶች ገቢ የሚያገኝበት መንገድ ነው።

ዜጎች በመነገድ፣ ቤት እና ንብረት በማከራየት፣ ዕውቀታቸውን በመሸጥ ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ ከሚያገኙት ገቢ ላይ በሕግ በተቀመጠው መሠረት ግብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

መንግሥትም የተሰበሰበውን ገቢ መልሶ ለኅብረተሰቡ ያለልዩነት አገልግሎት እና መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ የማዋል ኀላፊነት አለበት። ይህንን ለማድረግ ከዜጎች ግብር ይሰበስባል።

በአማራ ክልል በ2016 በጀት ዓመት 71 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 58 ነጥብ 3 በመቶ ማሳካት መቻሉን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ መረጃ ያሳያል። በ2017 በጀት ዓመትም የ2016 በጀት ዓመት እቅድ ለማሳካት ወደ ሥራ ተገብቷል።

ሐምሌ/2016 ዓ.ም የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የተጣለባቸውን ግብር እንዲከፍሉ ተደርጓል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን ሀርቡ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪ የኾኑት ግብር ከፋይ ይገኙበታል።

ግብር ከፋዩ ከ1992 ጀምሮ ከንግድ ሥራ ከሚያገኙት ገቢ፤ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ከመድኃኒት ቤት ከሚያገኙት ገቢ በደረሰኝ እንዲሁም የአከራይ ተከራይ ግብር እየከፈሉ ይገኛል።

ባለፈው በጀት ዓመት 72 ሺህ ብር መክፈላቸውን ያነሱተሰ ግብር ከፋዩ በሐምሌ ወር ደግሞ ከኪራይ ገቢ 11 ሺህ ብር ከፍለዋል። በዚህ ወር መጨረሻ ደግሞ የሚጣልባቸውን ግብር እንደሚከፍሉ ገልጸዋል።

ግብር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት እንዲስፋፋ መሠረታዊ ጉዳይ በመኾኑ በኀላፊነት እየከፈሉ መኾኑን ገልጸዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ የሚሠሩ መሠረተ ልማቶች የአካባቢው ማኅበረሰብ ግብርን ቀድሞ እንዲከፍል አንድ መልካም እድል መፍጠሩን አንስተዋል።

“ግብር መክፈል ማኅበረሰቡ በተናጠል ሊሠራው የማይችለውን ሥራ በመንግሥት አማካይነት እንዲሠራ ኀላፊነት መስጠት ማለት በመኾኑ ግብር ከፋዩ የተጣለበትን ግብር በወቅቱ እና በቅንነት ሊከፍል ይገባል፤ በራስ አቅም ለመልማት ግብርን በወቅቱ መክፈል ባሕል ሊኾን ይገባል” ብለዋል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፍቅረማርያም ደጀኔ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ 359 ሺህ 057 የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግዴታቸውን ይወጣሉ ተብለው ከተለዩት 262 ሺህ 735 ግብር ከፋዮች ውስጥ 209 ሺህ 906 የሚኾኑት በሐምሌ ወር ያለምንም ቅጣት እና ወለድ ግብራቸውን ከፋለዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 165 ሺህ 193 የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ሲኾኑ 44 ሺህ 713 ደግሞ የኪራይ ገቢ ግብር ከፋዮች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ 18 ሺህ 806 የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎች ሪፖርት ማድረግ የሚጠበቅባቸው ግብር ከፋዮች እንዳሉ ያነሱት ኀላፊው በአዲሱ አዋጅ መሠረትም ሐምሌ ወር ላይ የተከናወኑ ግብይቶች እስከ ጳጉሜን 05/2016 ዓ.ም እንዲሁም ነሐሴ ውስጥ የተካሄደን ግብይት እስከ መስከረም 30/2017 ዓ.ም ሪፖርት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

ግብር ከፋዮች ለአላስፈላጊ ቅጣት እና ወለድ እንዳይዳረጉ ሕጉን ተከትለው በተቀመጠው ጊዜ በየደረጃው በሚገኝ የገቢ ተቋም ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ሁሉም ለገቢ አሰባሰቡ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የክልሉ የአገልግሎት ዘርፍ ፍኖተ ዕቅድ ሰብዓዊ ካፒታልን መገንባት ዓላማ ያለው ነው” የኢኮኖሚ አማካሪው ሰኢድ ኑሩ (ዶ.ር)
Next articleየፍትሕ ሥርዓቱ ራሱን እንዲፈትሽ ተጠየቀ።