“የክልሉ የአገልግሎት ዘርፍ ፍኖተ ዕቅድ ሰብዓዊ ካፒታልን መገንባት ዓላማ ያለው ነው” የኢኮኖሚ አማካሪው ሰኢድ ኑሩ (ዶ.ር)

34

አዲስ አበባ: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የትውልድ ቁጭት ለትውልድ ልዕልና የማነጽ የ25 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድን በተመለከተ ከባለሃብቶች ጋር ውይይት ተካሒዷል።

በውይይቱ ወቅት የልማት ዕቅዱ አስተባባሪ እና ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪው ሰኢድ ኑሩ (ዶ.ር) እንዳሉት የክልሉ ሕዝብ በጦርነት እና አለመረጋጋት ውስጥም ኾኖ ኢኮኖሚው ፅኑ እና ችግር የሚቋቋም ኾኖ ቀጥሏል።

የበአማራ ክልል የከተሜነት ዕድገት ፍጥነት በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል የሚሉት ዶክተር ሰኢድ ግብርና ያለውን የሰው ኀይል የመሸከም አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ በመኾኑ ሌሎች ዘርፎችን ማሳደግ አሰገዳጅ ነው ብለዋል።

በዚህም የአገልግሎት ዘርፉ በአጠቃላይ ያለው አቅም እና የሰው ኀይል የመሸከም ሁኔታ መጨመር አለበት ነው ያሉት።

አዝጋሚ ዕድገት መኖር እና ዝቅተኛ ምርታማነት በአገልግሎት ዘርፉ የቁጭት ዕቅድ እንዲኖር መነሻ ምክንያት ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡

በ2042 የአማራ ክልል በዓለም ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ የኾነ የዘመናዊ ኢኮኖሚ አቅም ባለቤት ኾኖ ማየት የሚለው የክልሉ የ25 ዓመት ዕድገት ፍኖት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የአገልግሎት ዘርፉ የራሱን ከፍተኛ ድርሻ እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል።

ከአገልግሎት አንጻር ሲታይ ከተሞች ገቢ የሚያመጡ ብቻ ሳይኾኑ ለመኖር ምቹ የኾኑ ከተሞችን መገንባትን ይጠይቃል።

ከክልሉ መሬት ውስጥ 3 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ ሰው የሚኖርበት እንደኾነ የሚያስቀምጠው ዕቅዱ ከተማው ከ1 በመቶ መሬት በታች እንደኾነ ያትታል። በዚህም ታሳቢ ተደርጎ የተሻሉ መኖሪያ አካባቢዎችን መገንባት ይፈልጋል ይላሉ።

በከተሞች ውስጥ የሆቴሎችን አቅም፣ ብዛት እና ስብጥር ማሳደግ፤ ብቁ ተወዳዳሪ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲኖሩ በማድረግ የቱሪስት ፍሰትን ማሳደግ የአገልግሎት ዘርፉ የያዛቸው ትልሞች ናቸው።

በንግድ እና ገበያ ልማት በኩል የክልሉን የንግድ መዋቅር ማዘመን እና የኢንዱስትሪው አካል ማድረግ እንደሚገባም ያስቀምጣል።

ትርፍን ከትንሽ ሽያጭ ሳይኾን ከብዛት ማግኘትን መሠረት ያደረገ እንዲኾን ማድረግ ለዚህም ዋና ዋና አቅራቢዎችን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ዶክተር ሰኢድ ገለፃ ዕቅዱ ከአስመጭዎች ይልቅ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የሚያከፋፍሉትን ማብዛት፤ ማሽነሪዎች እና መገንቢያዎችን የሚያስገቡትን ማብዛት መሠረት ያደረገ ስለመኾኑም ገልጸዋል።

ትምህርት እንደ ማኅበራዊ ግብ ተወስዶ እንደ ፍትሐዊ የሃብት ክፍል ማሳያ እንዲኾን ማድረግ ያስፈልጋልም ባይ ናቸው። ትምህርት ዋና የሰብዓዊ ካፒታል ኾኖ የዕድገት ምንጭ እንዲኾን ታሳቢ ያደረገም ስለመኾኑ አስገንዝበዋል፡፡ ነገን የምናየው በትምህርት መኾኑን ያመነ ዕቅድ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።

ጤናን የመጨረሻው ማኅበራዊ ግብ ያደረገ የአገልግሎት ዘርፍ ዕቅድ ስለመታቀዱ የሚናገሩት ዶክተር ሰኢድ በዚህም ኮንቬንሽናል አረዳድ ያለው እና ርትዕ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ ስለመኾኑ አንስተዋል።

ምርታማ እና ቅልጥፍናን መሠረት ላደረገው የኢኮኖሚ ዕድገት የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ዘርፉ ስትራቴጂካል ድጋፍ እንዲያደርግ ማስቻል ሌላው ጉዳይ መኾኑን አስረድተዋል።

ኢንደስትሪያላዊነትን የሚመጥን ክልላዊ ሎጀስቲክስ መገንባት እንዲሁም ፈጣን የከተማ ዕድገት እና ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን አንቅስቅሴ እና የግብዓት እቅርቦት ማቀላጠፍ የሚያስችል ማድረግም እንደሚጠበቅ ነው የጠቆሙት።

ደረቅ ወደብ በክልሉ ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያለውን ድርሻ በአግባቡ እንዲወስድ እንዲሁም አገልግሎቱ እንዲያድግ ማድረግ ይገባል ብለዋል። የቀጣናው የፖለቲካ እና የአካባቢው ሀገራት እንቅስቃሴ ከኢኮኖሚው ጋር ትስስር ያለው በመኾኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article
Next article“በራስ አቅም ለመልማት ግብርን በወቅቱ መክፈል ባሕል ሊኾን ይገባል” ግብር ከፋይ