ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የበሽታዎች ቁጥጥር እንዲከናወን ተጠየቀ፡፡

45

ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ድንገተኛ የጤና አደጋ ስጋት ምላሽ ጋር የወባ በሽታ መከላከል ተግባራት ላይ በቅንጅት እየሠሩ መኾኑን ባካሄዱት ውይይት ገልጸዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ሥራ አሥፈጻሚ እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ ተቋማት በጋራ የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራን አጠናክረው መቀጠላቸው ነው የተብራራው፡፡

በውይይቱም የሁሉም ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊዎች የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራዎች በክልሎች ደረጃ እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች አቅርበው ተገምግሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ እንደተናገሩት ኅብረተሰቡ የራሱን ጤና ለመጠበቅ እና የወባ በሽታን ለመከላከል መሠራት አለበት፡፡

ዶክተር መሳይ በክርምቱ ወቅት ከሚደረጉ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ጋር የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወን እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የድንገተኛ ጤና አደጋ ስጋት ምላሽ ማስተባበሪያ ኀላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ አሁን ካለው በላይ የወባ በሽታ ስርጭትን የሚያባብሱ ምክንያቶች እየጨመሩ የሚመጡ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

ዶክተር መልካሙ በቀጣይ ከትምህርት ቤቶች መከፈት ጋር በተያየዘ ተማሪዎች የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ዶክተር ህይዎት ሰሎሞን የቤት ውስጥ የጸረ ወባ ኬሚካል እርጭት በአብዛኛው ወባማ በኾኑ አካባቢዎች መካሄዱን አስረድተዋል፡፡

ዶክተር ህይዎት የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስ አንዱ እና ዋነኛው ተግባር የወባ ትንኝ ቁጥጥር ሥራዎችን መሥራት በመኾኑ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የልጆቻችንን እንባ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማበስ ቆርጠን መነሳት ያለብን ጊዜው አሁን ነው” የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉደይ ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)
Next articleየማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮችን እንዴት እንጠቀም?