
አዲስ አበባ: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉደይ ሚኒስቴር ያለ እድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል በተሠራው ሥራ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረቱ አካላት እውቅና ሰጥቷል።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉደይ ሚንስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በንግግራቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያለእድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን የማስቆም ብሔራዊ ጥምረት በማቋቋም እና ሰፋፊ የማኅበረሰብ ንቅናቄዎችን በማካሄድ በተቀናጀ አግባብ ሲመራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በተቀናጀው ጥረትም በርካታ ሕጻናት እና አፍላ ወጣት ሴቶች ከዚህ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ወንጀል ከኾነው ያለእድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛት መታደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ጥረታችን ፍሬ እያፈራ ቢኾንም ጉዟችንን ገና አላጠናቀቅንም፤ ያሉት ሚንስትሯ ዛሬም የፍትህ አካላትን ጠንካራ እርምጃ፣ የጤና እና የትምህርት ሴክተሩን ርብርብ፣ የሃይማኖት አባቶችን ቁርጠኝነት፣ የአጋር አካላትን ድጋፍ፣ የሲቪል ተቋማትን ማኅበረሰባዊ አንቀሳቃሽነት እንፈልጋለን ብለዋል።
በጥምረቱ ስኬት ዓለም አቀፍ እውቅ እና በመገኘቱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የማኅበራዊ ልማት፣ የጤና፣ የባሕል እና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ ይህ ዓለም አቀፍ እውቅና በቅንጅት መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።
ያለ ዕድሜ ጋብቻን እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረትም ሁላችንም ኀላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ሲሉ በመድረኩ ተናግረዋል።
ያለእድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም እንዲያስችል የአምስት ዓመት ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እና ጸድቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ የተሸጋገረው የጥምረቱ የሥራ እንቅስቃሴ ዘንድሮ አምስተኛው ዓመት ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል በሠራችው ሥራ ባለፈው ወር በኒዎርክ በተካሄደው መድረክ በተባበሩት መንግስታት እውቅና ማግኘቷ ይታወሳል።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!