
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አልሚ ባለሃብቶች በዞኑ ያለውን እምቅ ሃብት በመጠቀም በኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲሰማሩ ምቹ እና ቀልጣፋ አሠራር እንደሚፈጥር የሰሜን ወሎ ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታውቋል።
መምሪያው የ2016 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 ዓ.ም የዕቅድ ትውውቅ አካሂዷል፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሞላ ደሱ የሰሜኑ ጦርነት በስምምነት ከተፈታ በኋላ የዞኑ ኢንቨስትመንት መነቃቃት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
በርካታ አልሚ ባለሃብቶች በዞኑ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎታቸው መጨመሩን የተናገሩት ኀላፊው በ2016 በጀት ዓመት በዞኑ 175 በላይ ለሚኾኑ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያገኙ አልሚ ባለሃብቶችም በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በምርት እና በአገልግሎት ዘርፍ ተሰማርተዋል። ከ5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸውን ኀላፊው አስረድተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ለአምራች ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት የሚውል 214 ሄክታር መሬት በሳይትፕላን እንዲመላከት ማድረግ ተችሏል። በዘርፉ የተሰማሩ አልሚ ባላሃብቶች 2 ሺህ 858 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉም ጠቁመዋል።
በያዝነው 2017 በጀት ዓመትም በርካታ ባለሃብቶችን ለመሳብ አሠራሮችን ቀልጣፋ የማድረግ እና የማዘመን ሥራ ታቅዶ እየተከናወነ መኾኑን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ አመላክቷል።
👉ባለሃብቱ ዕውቀቱን፣ ገንዘቡን እና መንግሥትን አምኖ ስለሚመጣ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ ማድረግ፣
👉የአካባቢውን ማኅበረሰብ የሚጠቅም ጥራት ያለው ፕሮጀክት የማስተናገድ
👉የዞኑን ጸጋ በማስተዋወቅ 240 አዳዲስ ኢንቨስተሮችን በመሳብ ፍስሰቱን መጨመር
👉ለ191 አልሚ ባለሃብቶች አዲስ ፈቃድ መስጠት እና
👉 በዘርፉ ለ28 ሺህ 255 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ዋና ዋና የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ ትኩረቶች መኾናቸውን መምሪያ ኀላፊው አብራርተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!