
ሰቆጣ: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በፋሽሽት ኢጣሊያ በተወረረች ጊዜ የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ከተዋደቁ ጀግኖች መካከል አንዱ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ናቸው።
ዋግ ኽምራ ካፈራቻቸው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አንዱ የኾኑት ሌትናንት ጀኔራል ኃይሉ ከበደ በወለህ ሜዳ ጠላትን ረምርመው የተሰው ጀግና ናቸው።
አባ መረብ ኃይሌ – ኃይሌ አባ ይባስ፣
አንገቱን የሰጠው አንደ ዮሐንስ፣
ወለህ ከሜዳው ላይ ገብቶ ሲቀድስ፣
ቄሱም ታጸረ ነው ዲያቆኑም ሞገስ።
ተብሎ የተገጠመላቸው ጀግና ናቸው።
በጀግንነት ከተሰው በኃላም አጼ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያውን የሌተናል ጀኔራልነት ማዕረግ የሰጧቸው ጀግና ናቸው።
የሻደይ በዓልን ምክንያት በማድረግ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ዙርያ ወረዳ በተሰውበት ወለህ ከተማ የስማቸው መታሰቢያ ሙዝየም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦላቸዋል።
የመሠረት ድንጋዩንም የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማ፣ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዳግም ባይነሳኝ እና የሰቆጣ ዙርያ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ እሚያምረው ጌጤ አስቀምጠዋል።
የመታሰቢያ ሙዚየሙም በ26 ሚሊየን ብር ወጭ እንደሚገነባ ተነግሯል።
ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!