የተዘነጉት እሴቶቻችን

42

ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገራችንም ኾነ በክልላችን በርካታ የተዘነጉ፣ ወደ ስርቻ የተጣሉ፣ ዘመነኛነት ያወየባቸው፣ የሌሎች ኩረጃ ያደበዘዛቸው፣ የአላዋቂነት መርግ የተጫናቸው እና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች የዘነጋናቸው እሴቶች አሉን፡፡ ለምን? ብለን አንጠይቅ ዘንድ “ዘመናዊነት” ይሉት ዘመናዊ ያልኾነ ምላሽ ይሰጠናል፡፡

በነሐሴ ወር ውስጥ ከሚከበሩት በዓላት መካከል የቡሄ (ደብረ ታቦር) የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላትን በወፍ በረር ልንቃኝ ወደድን። የቡሄ በዓል የክረምቱ ወራት መገባደዱን ተከትሎ ወንድ ሕጻናት የቡሄ ጅራፋቸውን እያስጮሁ፣ በሆያ ሆዬ ጭፈራቸው ብስራት የሚያሰሙበት እና የአብሮነት ፍቅራቸውን አብሮ በመጨፈር እና አብሮ በመብላት የሚገልጹበት ነው፡፡

የቡሄ (ደብረ ታቦር) በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊት ያለው ሲኾን የዚህ ትዝብት ማጠንጠኛው ግን የሕጻናቱ ጅራፍ ማጮህ፣ የሆያ ሆዬ ጭፈራ እና ተዛማጅ ክዋኔዎች ላይ ነው።

እስኪ ከተማ ውስጥ ላደጉ ሕጻናት ጅራፍ ምንድን ነው? ከምንስ ይሠራል? ለምን አገልግሎትስ ይውላል? በሉና ጠይቋቸው፡፡ የሚሰጧችሁ መልስ ‘አላውቀውም’ የሚል እንደሚኾን ባልጠራጠርም ላለማወቃቸው ተጠያቂዎቹ ግን ሕጻናቱ ብቻ ሳይኾኑ ወላጆቻቸውም ጭምር ናቸው፡፡

ስለ ቡሄ ጅራፍ የማያውቁት እና ጅራፍ ቢሰጣቸው ራሳቸውን የሚገርፉት ዘመነኞቹ ሕጻናት (መዘመን የራስን እሴት እየደፈጠጡ ከኾነ ማለቴ ነው) ዕድሜ ጠገብ አዛውንቶችን ከፍተኛ ድምጽ በሚያሰሙ ተቀጣጣይ ነገሮች (ሮኬቶች) ማስደንገጡ ላይ ግን የሚቀድማቸው የለም። ጅራፍ ማስጮህ ሳይችሉ በየቦታው የሚጮህ ነገር እያፈነዱ የአካባቢን ሰላም በማወክ ደስታን የሚገበዩ ሕጻናትን ዘምነው ነው ብትሉኝ እኔ አልስማማበትም፡፡

እስኪ ከነባሮቹ የሆያ ሆዬ ስንኞች ጥቂቶቹን መዝዤ አሁን ላይ ከተማ ውስጥ ከሚደመጡት ጋር ታመዛዝኗቸው ዘንድ ልጋብዛችሁ፡-

ሆያ ሆዬ ሆ!
እዚያ ማዶ፣ ጢስ ይጤሳል
አጋፋሪ ይደግሳል
ያንን ድግስ፣ ውጬ ውጬ
ከድንክ አልጋ፣ ተገልብጬ
ያቺ ድንክ አልጋ፣ አመለኛ
ያለአንድ ሰው፣ አታስተኛ…
እያሉ በሽመል መሬት እየደቁ፣ በሚያምር ዜማ እና ትርጉም በሚሰጡ ስንኞች ቤት ለቤት እየዞሩ ይዘፍናሉ፡፡
የኔማ እከሌ፣ የሰጠኝ ሙክት
እግምባሩ ላይ፣ አለው ምልክት
መስከረም ጠባ፣ እሱን ሳነክት
የኔማ እከሌ፣ የፈተለችው
ሸማኔ ጠፍቶ፣ ማርያም ሠራችው
ለዚያች ለማርያም፣ እዘኑላት
ዓመት ከመንፈቅ፣ ወሰደባት…
የሚሉና ሌሎች መወድሶች እያቀረቡ ሲዘፍኑ ከቆዩ በኋላ ሽልማት እና ከዓመት ወደ ዓመት ያድርሳችሁ የሚለውን የወላጆች ምርቃት ከተቀበሉ በኋላ እነሱም፡-
ከዓመት እስከ ዓመት ድገምና
የነ እከሌን ቤት ድገምና
ወርቅ አዝንብበት ድገምና
ክበር በስንዴ፣ ክበር በጤፍ
ምቀኛህ ይርገፍ፣ እንደ ቆላ ወፍ
ብለው የሕጻን ምርቃታቸውን ያቀርባሉ፡፡

በዚህ ውስጥ ያለው የሕጻናቱ እና የወላጆቻቸው መከባበር ብቻ ሳይኾን አብሮነት እና የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት ከክረምቱ ባሻገር የሚመጣው የፀደይ ወር የአዕምሮ ስንቅ አይኾንም ብሎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡

አሁን ላይ በከተሞች ውስጥ የሚታየው የሆያ ሆዬ ጭፈራ ገንዘብ ከመለመን የዘለለ ትውፊትን የማስቀጠል ዝንባሌ እንደ ሌለው ከሕጻናቱ የሆያ ሆዬ ስንኞች መረዳት ይቻላል፡፡

ሆያ ሆዬ ሆ!
እዚያ ማዶ፣ አቦካዶ
እዚህ ማዶ፣ አቦካዶ
የኔማ እከሌ፣ ሮናልዶ
እዚያ ማዶ፣ አንድ ካልሲ
እዚህ ማዶ፣ አንድ ካልሲ
የኔማ እከሌ፣ ሊዮኔል ሜሲ
እና መሰል ስንኞች እየተደረደሩ በቅጡ ባልተቃኘ የሆያ ሆዬ ዜማ በየቤቱ ልመናው ይደራል።

ለእነዚህ ልጆች በባሕላችን መሠረት ብሎ ሙልሙል ዳቦ የሚሰጥ ሰው ቢገኝ የስድብ መዓት የሚወርድበት ከመኾኑም በላይ ቤቱ በድንጋይ ሊወገርም ይችላል፡፡

እነዚህ ስንኞች ዘመኑን የሚመስሉ እና የልጆቹን ፈጠራ የሚያሳዩ ናቸው ብሎ የሚሞግተኝ ሰው ካለ ለምን በሀገራችን ውስጥ ጀግኖችን ሳናጣ የውጭ እግር ኳስ ተጨዎቾችን ስም ማንሳት አስፈለጋቸው? የሚል ጥያቄ አቀርባለሁ፡፡

አጼ ምኒልክ፣ አጼ ቴዎድሮስ፣ በላይ ዘለቀ፣ አብዲሳ አጋ እና ሌሎችም ሀገራዊ ጀግኖቻችን በሕጻናቱ ስለማይታወቁ ወይስ እኛም ስላልነገርናቸው? እያልኩ በርካታ ጥያቄዎችን ማቅረብ እችላለሁ እና መፍትሄው በጋራ ከስህተታችን መመለሱ ላይ ነው ባይ ነኝ፡፡

በዚሁ በነሐሴ ወር ውሰጥ የሚከበሩትን የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓሎችም በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከሚለው እሳቤ ወጥተን በዓላቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚፈጥሩትን የአብሮነት ሥነ ልቦና ማስቀደሙ ጠቃሚ ነው። በእነዚህ በዓላት ሴት ሕጻናት በፆታቸው ከሚደርስባቸው የነፃነት ማነቆ ተላቀው በአደባባይ ደስታቸውን የሚያውጁበት በመኾኑ በዓሉን ለሴቶቻችን የነፃነት ማክበሪያነት ብናውለውም ፋይዳው ይጎላል፡፡

የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት በስፋት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች ወጥተው በትላልቅ ከተሞች ለአብነትም በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ መከበራቸው በዓላቱ እንዳይዘነጉ ከማስቻሉም በላይ በሕዝቦች ዘንድ የሚፈጥረው ትሥሥር በወሰን የማይለካ ነው። ትኩረት ተነፍጓቸው እየከሰሙ ላሉት በርካታ እሴቶቻችን መከበርም የእነዚህ በዓላት በስፋት መከበር የማንቂያ ደወል እንደሚኾንም አስባለሁ፡፡

“የራስን ጥሎ፣ የሰው አንጠልጥሎ” ይሉት የአበው ብሂል በሁሉም እሴቶቻችን ላይ ከመንፀባረቁ በፊት ለመንቃት ጊዜው አልረፈደብንም፡፡

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዋጋ በሚጨምሩ፣ በሚከዝኑ እና በሚያሸሹ አካላት ላይ እርምጃ እየወሰደ መኾኑን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next articleበኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሌተናል ጀኔራል የመታሰቢያ ሙዝየም የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።