
ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ዋጋ በሚጨምሩ፣ በሚከዝኑ እና በሚያሸሹ አካላት ላይ እርምጃ እየወሰደ መኾኑን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ከጀመረች በኋላ ለነዋሪዎች አስቸጋሪ ኾኖ የቆየው የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ አዝማሚያዎች ተስተውለዋል፡፡ የዶላር ምንዛሬው ከተመን ወጥቶ ገበያው ይወስነው ከተባለ በኋላ በጥሬ እቃዎች እና በሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ፣ ሃብት መሰወር እና ሌሎች የሕዝብን ኑሮ የሚያከብዱ አዝማሚያዎች ተስተውለዋል፡፡
መንግሥት የተደረገውን ማሻሻያ ሰበብ በማድረግ አላስፈላጊ የንግድ ሥርዓት ውስጥ የሚገቡ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮም የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የሚፈጠሩ ሕገ ወጥ የንግድ ሥርዓቶችን እንደሚቆጣጠር፣ የግንዛቤ ፈጠራ እንደሚሠራ እና ሕጉን ተላልፈው በተገኙ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ማስታወቁን ዘግበናል፡፡
የአማራ ክልል የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትገበራ ማግሥት ጀምሮ ችግሮች መስተዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ግንኙነት በሌለበት ሁኔታ ዋጋ መጨመር መከሰቱንም ገልጸዋል፡፡
የዋጋ ጭማሪው ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ብቻ ሳይኾን በሀገር ውስጥ በሚመረቱ የሰብል፣ እንሰሳት፣ አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም በሀገር ውስጥ በሚመረቱ የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይም ጭምር መኾኑን አመላክተዋል፡፡
ምርት እያለ የለም በሚል ለመሸጥ አለመፈለግ፣ ተሽጧል፣ ዋጋ አልወጣለትም በሚል ለመሸጥ ፈቃደኛ አለመኾን፣ ምርትን መደበቅ፣ ምርትን ከመደበኛ መሸጫ ቦታው ውጭ ማሸሽ እና ሌሎች የተስተዋሉ ችግሮች መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡
በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የምርት ዝውውር አለመኖር፣ ተጨማሪ ምርት ወደ ገበያው በስፋት አለመግባት፣ በሸማቹ ማኅበረሰብ በኩል የመደራደር አቅሙ ደካማ መኾን፣ ምርት ሊጠፋ እና ነገም ዋጋ ሊጨምር ይችላል በሚል ስጋት በብዛት መግዛት፣ ሊበላሹ የሚችሉ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና አትክልት ጭምር ተሰልፎ ተገቢ ባልኾነ ዋጋ የመግዛት ፍላጎት መኖር ከገጠሙ ዋና ዋና ችግሮች መካከል መኾናቸውን ነው ያመላከቱት፡፡
የገጠሙ ችግሮችን ለመፍታት መጀመሪያ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻያው ምንነት እና ፋይዳ፣ ለዝቅተኛ ነዋሪዎች እና ለንግዱ ማኅበረሰብ ያለው ጠቀሜታ፣ ማሻሻያው ከምርቶች ዋጋ ጋር አለመገናኘቱን እና የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ መኾኑ የሚያስገኘው ጠቀሜታ በተመለከተ ሰነድ አዘጋጅተው ለንግዱ ማኅበረስብ፣ ለሸማቾች፣ ለባለድርሻ አካላት እና ለሚዲያ ሰዎች ግንዛቤ ተፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
ነጋዴዎች የመሸጫ ዋጋ ዝርዝር እንዲለጥፉ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ ሸማቾች የመሸጫ ዋጋውን እንዲያውቁ፣ ችግር ሲኖር ደግሞ ጥቆማ እንዲያደርሱ መመቻቸቱንም ተናግረዋል፡፡ የተቀመጠውን መመሪያ ተላልፈው ዋጋ በሚጨምሩ፣ በሚከዝኑ እና በሚያሸሹ አካላት ላይ አሥተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡
የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 5 ሺህ 269 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል፡፡ እርምጃ ከተወሰደባቸው ነጋዴዎች መካከል 3 ሺህ 589 ነጋዴዎች ማስጠንቀቂያ፣ 1 ሺህ 643 ነጋዴዎች የድርጅት እሸጋ፣ 11 ነጋዴዎች የፈቃድ እገዳ እና 26 ነጋዴዎች ደግሞ በእስራት እንዲጠየቁ ኾኗል ነው ያሉት፡፡
598 ነጋዴዎች ምርት ከዝነው መገኘታቸውን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው 330 ነጋዴዎች ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው 268 ነጋዴዎች ደግሞ ድርጅታቸው እንዲታሸግ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ የተቋቋመው ግብረ ኀይል በቅንጅት እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
በገበያው ላይ ተጽዕኖ ከሚፈጥሩ የንግድ እና ግብይት ተዋንያን ጋር ተቀራርቦ መሥራት ይጠበቃል ያሉት ምክትል ኀላፊው በተለይም ከአምራቾች፣ ከጅምላ ነጋዴዎች፣ ከአስመጭዎች እና ከልማት ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ገበያውን በማረጋጋት ምርት በስፋት እና በጥራት እንዲያስገቡ፣ ገበያውን እንዲያጠግቡ የሚያስችል አቅርቦት መር የግብይት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡
ግብረ ኀይሉን በማጠናከር የቅንጅት ሥራውን ማሻሻል እና አጥፊዎች ላይ አስተማሪ የእርምት እርምጃ እየወሰዱ መቀጠል፣ አማራጭ የግብይት ማዕከላትን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ አምራች እና ሸማች በቀጥታ የሚገናኙባቸው የገበያ ማዕከላትን መገንባት እና ወደ ሥራ ማስገባት፣ የእሑድ ገበያዎችን በስፋት ማቋቋም፣ የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር ሸማቹ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኝባቸውን አማራጮች ማስፋፋት በቀጣይ መፍትሔ የሚኾኑ ሥራዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ማኅበረሰቡ መጀመሪያ አካባቢ ከነበረው መደናገር እና ምርት በሚጠራበት ዋጋ ከመግዛት ወጥቶ አጥፊ ነጋዴዎችን የመጠቆም እና ተረጋግቶ የመሸመት ሥራው እየተሻሻለ መጥቷል ነው ያሉት፡፡ ነገር ግን አሁንም በሚፈለገው ደረጃ አለመድረሱንም አመላክተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በፀጥታ ችግር ምክንያት የምርት ዝውውር የተሳለጠ አለመኾን ማኅበረሰቡ በሚፈልገው ደረጃ እንዳይኾ እንዳስገደደውም አንስተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!