
ሰቆጣ: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ሻደይ ባሕላችን ለዘላቂ ሰላማችን እና አንድነታችን” በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ 16 እስከ 21 ድረስ በብሔረሰብ አስተዳደር ደረጃ በሰቆጣ ከተማ በድምቀት ይከበራል።
የሻደይ በዓል በድምቀት ሲከበር ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር ከመፍጠሩም ባሻገር በወቅታዊ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የንግድ ልውውጥ እንደሚያጠናክረው የሰቆጣ ከተማ ነጋዴዎች ተናግረዋል።
አቶ ቴዎድሮስ ጨርቆሴ በምግብ ቤት አገልግሎት የተሰማሩ ሲኾኑ የሻደይን በዓል ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የዋግ ሕዝብ እንግዳ አክባሪ እና እንግዳ ተቀባይ ነው ያሉት ደግሞ በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ከፍያለው ግርማ ሲኾኑ ለዚህም ሆቴሎችን በማዘጋጀት እና ለእንግዶች ምቹ በማድረግ ተሳታፊዎቹን እየጠበቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላሽ ወርቃለም የከተማው የንግዱ ማኅበረሰብ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ምክክር እንዳደረጉ ገልጸዋል።
ይህንንም የሚከታተል ኮሚቴ እንዳዋቀሩ የገለጹት ከንቲባው ለሻደይ የሚመጡ እንግዶች በአግባቡ የሚስተናገዱበትን ምቹ ኹኔታ መፍጠራቸውንም ገልጸዋል።
“ዋግኽምራ ላይ ያለው አንጻራዊ ሰላም የሻደይን በዓል በተረጋጋ መንፈስ እንድናከብር ያግዘናል” ያሉት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኀላፊ አብርሃ ጌታወይ የጸጥታውን ዘርፍ በማጠናከር ከወጣቱ ጋር በቅርበት እየሠሩ እንደኾነ ተናግረዋል። እንግዶችም በሰላም ገብተው እስኪወጡ የከተማው ማኅበረሰብ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቆም የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ጣምተው ገላስ በበኩላቸው የሻደይን በዓል በሰቆጣ ከተማ በድምቀት ለማክበር በሁሉም ዘርፍ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። ተቋማቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!