“መሪዎች ሰላሙን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን እየሠሩት ያለው የልማት ሥራ የሚያሥመሠግን ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

28

ደሴ: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክትል ርእስ መሥተዳድር እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተመራ ልዑክ በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተመልክቷል። የልዑካን ቡድኑ አባላት ኮምቦልቻ ሰላሟን አስጠብቃ እየሠራች ያለችው የልማት ሥራ ለሌሎች አርዓያ የሚኾን ነው ብለዋል።

የኮሪደር ልማትን፣ የመንገድ ሥራን፣ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ የተሠራ የከተማ አሥተዳደሩ ሕንፃ፣ በ2016 ወደ ሥራ የገቡ ፋብሪካዎችን እና የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የተጀመረው የኮሪደር ልማት እና የመንገድ መሠረተ ልማቱ የሚበረታታ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በተለይ ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል የሚሠራው ፋብሪካ የተሻለ ተሞክሮ የታየበት መኾኑን አንስተዋል።

ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ “መሪዎች ሰላሙን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን እየሠሩ ያለው የልማት ሥራ የሚያሥመሠግን ነው” ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ በተመለከቷቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

“መሪዎች በዚህ ፈታኝ ወቅት ሰላሙን አስጠብቀው ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን መሥራታቸው የሚያሥመሠግን ነው” ብለዋል።
ባለሃብቶች እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተመልክተናል ያሉት የምክር ቤት አባላቱ የተሠሩት ሥራዎች ኅብረተሰቡን ያሳተፉ መኾናቸው የሚበረታታ መኾኑንም አንስተዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንድወሰን ልሳነወርቅ በተደረገው የመስክ ምልከታ ከተማዋ ያለችበትን ቁመና በማሳየት ከመሪዎች እና ከምክር ቤት አባላቱ ጋር ውጤታማ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።

ዘጋቢ:- አበሻ አንለይ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢንዱስትሪ ፓርኮች የዕውቀት ሽግግር እና ማኅበረሰባዊ አገልግሎት እንዲሰጡ መሥራት ይጠይቃል” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)
Next articleየኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ።