
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደብረ ብርሃን ኢንደስትሪ ፓርክ ከተመሰረተ ጀምሮ የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ ቀልጣፋና አመቺ የኢንቨስትመንትና የንግድ ሁኔታ ለመፍጠር የሄደበት ሥራ አበራተች መኾኑን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ገለጹ።
ኢንደስትሪ ፓርኩ እስከ አሁን የሠራቸውን ሥራዎች በማላቅ ሌሎች የተዘጋጁ ሼዶች ለባለሀብቶች በማስተላለፍ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚኾኑ በአከባቢው የሚገኘውን ከፍተኛ ምርት ለመጠቀም ገጠሩና ከተማውን ማስተሳሰር ያስፈልጋል ብለዋል።
ዶክተር አሕመዲን ደብረ ብርሃን የኢንደስትሪ ከተማ ነች ብለዋል። ፓርኩ ከደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ለተሻለ ምርታማነትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ውስጥ የራሱን አበርክቶ ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።
የክልላችን መንግሥት እና የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ለፓርኩ አስገፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፣ የከተማው እና የአከባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲኾኑ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
ዶክተር አሕመዲን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባጋሩት መልእክት በ6ኛ ዙር የዘንድሮ ሰባት ቢሊየን አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አካል የኾነውን አሻራችን በፓርኩ አኑራናል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!