የአውሮፓ ኅብርት እና ዩኒሴፍ የሕክምና መሳሪያዎች እና መድኃኒቶችን ለአምስት ክልሎች ድጋፍ ማድረጋቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

24

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኬር ፎር ሄልዝ ከሦስት ዓመት በፊት በአውሮፓ ኅብረት፣ በዮኒሴፍ እና በጤና ሚኒስቴር ትብብር የተቋቋመ ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ በድርቅ እና በግጭት የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ድጋፍ የሚያደር ሲኾን አምስት ክልሎች ላይ ድጋፉን ያደርጋል።

በድጋፉም መሠረት የኅብረተሰቡን ጤና ለማስጠበቅ እና የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚረዳ የህክምና መሳሪዎች እና መድኃኒቶችን ጤና ሚኒስቴር ከአውሮፓ ኅብረት እና ከዩኒሴፍ ተረክቧል።

ድጋፉ ለሕክምና የሚውሉ ቁሳቁሶች ሲኾኑ ኮምፒውተር፣ ቴሌቪዥን፣ ታብሌት፣ መድኃኒት እና ወባን ለመከላከል የሚረዳ አጎበር መኾናቸው ነው የተገለጸው፡፡

ድጋፉ በግጭቱ ለተጎዱ ጤና ጣቢያዎች እናቶች እና ሕጻናት እንዲሁም ለጤና ባለሙያዎች እንደሚውል የተናገሩት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ለድጋፉ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ የተደረገበት መኾኑን ገልጸዋል።

ዮኒሴፍ ለኢትዮጵያ መንግሥት በዘላቂነት የጤና መሳሪያ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ያነሱት የዩኒሴፍ ተወካይ አቡበከር ካምፖ ድጋፍ የጤናውን ሴክተር መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

ለድጋፉ ምሥጋና ያቀረቡት የተለያዩ ክልሎች የጤና ቢሮ ኀላፊዎች በድጋፉ የቀረቡ የጤና መሳሪያዎችን እና መድኃኒቶችን ለተጎዱ አካባቢዎች ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።

የተረከቧቸው የህክምና መሳሪያዎች እና መድኃኒቶች በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአፋር፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በግጭት ምክንያት ለተጎዱ የጤና ተቋማት እና ሆስፒታሎች በእርዳታ የሚሰጡ መኾናቸው ተጠቅሷል፡፡

ዘጋቢ፡- ራሄል ደምሰው

Previous articleየሻደይ በአልን ምክንያት በማድረግ በሰቆጣ ከተማ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
Next article“ፓርኩ ከደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ለተሻለ ምርታማነትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የራሱን አበርክቶ ሊወጣ ይገባል” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)