የኮምቦልቻ ከተማን የውኃ ችግር ይፈታል የተባለው ፕሮጀክት!

21

ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር እየተከናወኑ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ውስጥ የኮምቦልቻ የመጠጥ ውኃ ግንባታ አንዱ ነው። ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተጠይቋል።

በኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ የኾኑት ተናኘ ወርቄ እንዳሉት በከተማ አሥተዳደሩ ያለው የውኃ መሥመር ለብዙ ዓመታት ያገለገለ ነው። በሚያጋጥም የመስመር ብልሽት ነባር የከተማው አካባቢዎች የውኃ መቆራረጥ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ነግረውናል። እስከ አራት ቀን ድረስ ውኃ እንደማይገኝ ነው ያነሱት። በተለይም ደግሞ ከፍተኛ ቦታ ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ችግሩ ይጎላል ብለዋል። አሁን እየተሠራ የሚገኘው የውኃ ፕሮጀክት ችግሩን ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅም ጠይቀዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሐመድአሚን የሱፍ ፕሮጀክቱ በሰሜኑ ጦርነት እና በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ቢቆይም አሁን በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ አሁን ላይ ያለውን 55 በመቶ የከተማውን የውኃ ሽፋን ወደ መቶ በመቶ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል። ይህ ደግሞ እየጨመረ የመጣውን ማኅበረሰብ እና የኢንዱስትሪውን የውኃ አቅርቦት ችግር ለቀጣይ 20 ዓመታት ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል። “በ2030 ዓ.ም የውኃ ሽፋንን መቶ በመቶ ማድረስ” የሚለውን ሀገራዊ አቅጣጫም ያሳካል ብለዋል።

የኮምቦልቻ መጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ ፕሮጀክት ተጠሪ መሃንዲስ ልመንህ ዋለ ፕሮጀክቱ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት፣ በቅየሳ እና በተቋራጩ ችግር ምክንያት ሥራው ሲጓተት መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም ዳግም ውሉን በማሻሻል 515 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ከየካትት/2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ተገብቷል። በ12 ወራት ጊዜ ውስጥም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። አሁን ላይ ከሚቆፈሩ አምስት ጥልቅ ጉድጓዶች አንዱ ተጠናቅቋል። የሌሎች ጥልቅ ጉድጓዶች የቁፋሮ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ከሁለቱ የውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ውስጥ ባለ 500 ሜትር ኪዩብ ጋን በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። ባለ 200 ሜትርኪዩብ ማጠራቀሚያ ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ከጥልቅ ጉድጓዶች ወደ ማጠራቀሚያ ጋኖች የሚወስደው 12 ኪሎ ሜትር የመሥመር ዝርጋታ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ከውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ወደ ማኅበረሰቡ ለማዳረስ ደግሞ 102 ኪሎ ሜትር የውኃ ማሰራጫ መሥመር ዝርጋታ ሥራ የሚሠራ ይኾናል። እስከ አሁን የ52 ኪሎ ሜትር የዝርጋታ ቁሳቁስ ማቅረብ ተችሏል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 48 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የመስመር ዝርጋታ ሥራ ተሠርቷል። አሁን ላይ አጠቃላይ ሥራው 48 ነጥብ 12 በመቶ መድረስ ቢኖርበትም በግብዓት አቅርቦት ችግር ምክንያት መድረስ የቻለው 28 ነጥብ 7 በመቶ ላይ እንደኾነ ገልጸዋል።

በተቋራጩ የሚነሳው ክፍያ እንዲለቀቅ እየተሠራ መኾኑን ያነሱት ተጠሪ ማህንዲሱ ክፍያው እንደተለቀቀ ግብዓት እንዲያቀርብ እና ሥራውን በተቀመጠው ጊዜ እና ጥራት እንዲጠናቀቅ ይደረጋል ብለዋል። አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ዘጠኝ ጥልቅ ጉድጓዶችን የሚያካትት ሲኾን አምስቱ የሚቆፈሩ፤ አራቱን ደግሞ የማገናኘት ሥራ የሚሠራ ይኾናል። ዘጠኙ ጉድጓዶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ በሰከንድ 367 ሊትር ውኃ ያመነጫሉ። ይህም አጠቃላይ የከተማውን የውኃ አቅርቦት በሰከንድ የማመንጨት አቅም ወደ 534 ሊትር ያሳድገዋል። ይህ የውኃ አቅርቦት መጠን እስከ 2030 ዓ.ም ድረስ 267 ሺህ ለሚኾን ሕዝብ የውኃ ፍላጎትን ማርካት ይችላል ተብሏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕጻን ሄቨን ጉዳይ የምርመራ፣ የክስ እና የፍርድ ሂደት እንዴት ነበር?
Next articleየሻደይ በአልን ምክንያት በማድረግ በሰቆጣ ከተማ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።