
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሕጻን ሄቨን በተፈጸመባት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሕይዎቷ ማለፉን በተመለከተ ከሰሞኑ በስፋት መነጋገሪያ ኾኗል፡፡ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በሕጻን ሄቨን ዓወት ጉዳይ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም የምርመራ፣ የክስ እና የፍርድ ሂደትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በሕጻኗ ላይ የተፈጸመው ወንጀል ከባድ፣ አሰቃቂ፣ ከማኅበረሰብ ባሕል፣ ወግ፣ እሴት እና ሃይማኖት በእጅጉ ያፈነገጠ፣ ሕዝብ እና መንግሥትን በእጅጉ ያስቆጣ ነው ብለዋል፡፡ ኀላፊው ልዩ ድጋፍ እና ጥበቃ የሚያስፈልጋት ልጅ ላይ እንዲህ አይነት ወንጀል መፈጸሙ እጅግ አሰቃቂ ሐዘን የሚፈጥር መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ሐዘኑ ለወላጆቿ ብቻ ሳይኾን የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ጭምር መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በሕጻኗ ላይ በተፈጸመው ድርጊት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘንም ገልጸዋል፡፡ የተፈጸመውን አጻያፊ ድርጊት በዕውነት፣ በመረጃ እና በትክክለኛ ሁኔታ ተመስርተው ላወገዙ እና ላገዙ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ጉዳዩ አሁን ላይ በፍርድ ቤት ክርክር ላይ በመኾኑ የሚሰጠው ማብራሪያ እና መግለጫ የፍርድ ሂደቱን እንዳይጫን እና በፍርድ ቤቶች ነጻነት ላይ ተጽዕኖ እንዳያደርስ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት፣ የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ፣ የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአማራ ፍትሕ ቢሮ ከምርመራ ሥራ እስከ ፍርድ ድረስ የሠሩትን መልካም ሥራ እና የተገኘውን መልካም ውጤት የሚያደበዝዝ እንቅስቃሴን ማጥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ወንጀሉ በ2015 ዓ.ም መፈጸሙን ያስታወሱት ኀላፊው የምርመራው ሂደቱ የተሠራው ወንጀሉ ከባድ፣ አጸያፊ፣ የአፈጻጸም ሂደቱ አሰቃቂ እና ወንጀሉ የተፈጸመባት ሕጻን በመኾኗ ዓለም አቀፍ ሕግ ለሕጻናት የሚሰጠውን መብት እና የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ለሕጻናት የሚሰጠውን ጥበቃ መሠረት ተደርጎ ምርመራው በልዩ ትኩረት መመራቱን አስታውሰዋል፡፡
ምርመራው በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አማካኝነት ሲመራ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ በምርመራ ሂደቱ የሰው፣ የሰነድ እና የሕክምና ማስረጃዎች በፍጥነት እና በጥራት ለማሠባሠብ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ የሕጻን ሄቨን እናት የምርመራውን ሂደት እንዲያግዙ፣ የምርመራ ሂደቱን እንዲረዱ፣ አስፈላጊ ሲኾን መረጃ እንዲጠቁሙ እና የምርመራውን ታማኝነት እንዲገነዘቡ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ላደረጉት ብርቱ እና ጥራት ያለው እገዛም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ጉዳዩ በምርመራ ላይ እንዳለ በክልሉ በተፈጸመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ወንጀሉን የፈጸመው ግለሰብ በሕግ ጥላ ሥር ከነበረበት ጣቢያ አምልጦ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ በሕጻን ሄቨን ላይ ወንጀል ከፈጸመው ሰው ጋር በሺዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች እና ፍርደኞች ማምለጣቸውን ያስታወሱት ኀላፊው የተፈጸመው ወንጀል ከባድ እና አሰቃቂ በመኾኑ መንግሥት ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት ተከሳሹን መልሶ በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ወንጀል የፈጸመው ግለሰብም ዋስትናው ተከልክሎ በማረሚያ ቤት ኾኖ ክሱን እንዲቀጥል መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ለዐቃቢ ሕግ ከደረሰ በኋላ ለተፈጸመው ወንጀል የሚመጥን ተገቢውን የሕግ ድንጋጌ በመጥቀስ በተከሳሹ ላይ ሁለት ክሶች መቅረባቸውን ነው የገለጹት፡፡ አንደኛው ክስ “አስገድዶ ሕጻንን በመድፈር፣ ሁለተኛው ደግሞ አስገድዶ ከደፈረ በኋላ ወንጀሉ እንዳይታወቅ ሕጻን ገድሏል” የሚሉ ክሶች መቅረባቸውን ነው ያስታወሱት፡፡
ዐቃቢ ሕግ ክስ ካቀረበ በኋላ ጥፋተኛ እስከሚያሰኝ ድረስ እጅግ ውስብስብ እና ጠንካራ የኾኑ ክርክሮችን ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡ ሂደቱ እጅግ ውስብስብ፣ ዕውቀት እና ድካምን የሚጠይቁ እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡
ዐቃቢ ሕግ በብቃት እና በጽናት ተከራክሯል ያሉት ኀላፊው ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ ጥፋተኛ እንዲኾን መደረጉን ነው የገለጹት፡፡ ዐቃቢ ሕግ አንድ የቅጣት ማክበጃ አቅርቧል፤ ተከሳሹ ደግሞ ሁለት የቅጣት ማቅለያ አቅርቧል፣ በዚህም መሠረት ጥፋተኛ የተባለበት የወንጀል ሕግ የሚያስቀጣው የዕድሜ ልክ ጽኑ እሥራት ነው፤ ነገር ግን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው የቅጣት አወሳሰን መሠረት ተከሳሹ ጥፋተኛ የተባለበት ደረጃው አንድ ወይም ከፍተኛ የሚባል ሲኾን እርከኑ ደግሞ 38 ነው ብለዋል፡፡
አንድ ማክበጃ ሲጨመር እርከኑ ወደ 39 ከፍ ይላል፣ ሁለት ማቅለያ ሲጨመር ደግሞ እርከኑ ወደ 37 ዝቅ ሊል ችሏል፤ በቅጣት አወሳሰኑ መመሪያ መሠረት እርከን 37 የሚያስቀጣው መነሻው 20 ዓመት መድረሻው 25 ዓመት ጽኑ እሥራት ነው፡፡ ዐቃቢ ሕግ የወንጀሉን ክብደት፣ አሰቃቂነት እና የሟችን ዕድሜ በማስረዳት የመጨረሻውን ጽኑ እሥራት በተከሳሹ ላይ እንዲወሰን አስደርጓል ነው ያሉት፡፡
ከቀረቡት ክሶች መካከል አንደኛው ውድቅ ኾኗል፡፡ አንዱ ክስ ውድቅ የተደረገው ሕጻኗን ከደፈረ በኋላ መድፈሩ እንዳይታወቅ የገደላት ስለመኾኑ ማስረዳት ስላልተቻለ ነው፣ ሞቱን ያመጣው መደፈሩ ነው፣ ሞቱን መደፈሩ ካመጣው አንደኛው ክስ ብቻ ነው ትክክል የሚኾነው፣ ደፍሮ መደፈሩ እንዳይታወቅበት ነው የገደላት ቢባል ኖሮ በሁለቱም ክስ ጥፋተኛ ይባል ነበር ነው ያሉት፡፡ ማስረዳት የተቻለው መደፈሯን እና መሞቷን ነው ብለዋል፡፡
ማስረጃ ማቅረብ ያልተቻለበት ክስ እስከ ሞት ድረስ ያስቀጣል ያሉት ኀላፊው ማስቀጣት የሚቻለው ግን በማስረጃ ሲረጋገጥ መኾኑን ነው ያመላከቱት፡፡ ቅጣት የሚሰጠው በተረጋገጠው እና ማስረጃ በተገኘበት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ውሳኔ የካቲት 2016 ዓ.ም ከተወሰነ በኋላ ውሳኔው ሕዝብ እና ሌሎች አጥፊዎች ከዚህ እንዲማሩበት የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጠው እና ፍትሕ ቢሮ ባዘጋጀው ዓመታዊ መጽሔቱ ላይ እንዲካተት በማድረግ ሕዝብ እንዲያውቀው ተደርጓል ብለዋል፡፡ ከክስ ሂደቱ እስከ ፍርድ አሰጣጡ ድረስ ሥራው በአግባቡ እንዲመራ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
የተሰጠው ፍርድ አንሷል፣ በዝቷል ወይስ በቂ ነው የሚለውን ከማየት እና ከመተቸት አስቀድሞ የሀገሪቱን ሕጎች መመርመር ይገባልም ብለዋል፡፡ በተጻፈው ሕግ መሠረት፣ ሀገሪቱ ባላት የወንጀል ሕግ እና የቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሠረት የሚቀመጠውን ቅጣት በማስላት ትልቁን እና ከፍተኛውን ጣሪያ ተቀጥቷል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ ሕዝብ ልዩ እገዛ በማድረግ የፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማ እና ተደራሽ እንዲኾን ማድረግ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡ በበቂ መረጃ ላይ ሳይመሠረቱ፣ ጉዳዩን በጥልቀት ሳይረዱ፣ የተሠራውን ሥራ፣ የነበረውን ውጣ ውረድ ሳይገነዘቡ የክልሉን መንግሥት እና የፍትሕ ተቋማት የሠሩትን መልካም ሥራ ጥላ እንዲያጠላበት የሚያደርጉ ጥቂት አካላት ወደ ቀልባቸው ተመልሰው መልካም እገዛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
ምስክሮች እና ጠቋሚዎች በወጣው የጥበቃ አዋጅ መሠረት ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡
የሕጻን ሄቨን እናት ማዋከብ እና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደኾነ የሰማነው ከሰሞኑ መገናኛ ብዙኀን ላይ ከወጡ በኋላ ነው፤ ለፍትሕ ቢሮው ያቀረቡት ነገርም የለም፤ ተጎድተው ሳለ በባሕር ዳር እንዳይቀመጡ የሚያደርጋቸው አካል ካለ መጥተው ቢያመለክቱ በሕግ አግባብ መጠየቅ እንችላለን፤ የምስክር እና የጥቆማ ጥበቃ እናደርግላቸዋለን ነው ያሉት፡፡
ተከሳሹ ጥፋተኛ እንዲባል ትልቅ እገዛ ማድረጋቸውንም አስታውቋል፡፡ ወከባ እና ማስፈራሪያ በሚያደርሱባቸው አካላት ላይ በሚቀርበው ማስረጃ መሠረት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ቢሮው ኀላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ግዴታችን ነው፤ እንዲመጡ ጥሪ እናቀርባለን ነው ያሉት፡፡ ለሕይዎታቸው አስጊ በሚኾኑ ጉዳዮች ላይ ከለላ ይሰጣልም ተብሏል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!