ፍትህ ጠያቂ ድምጾች

97

ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰውዬው የሕግ ትምህርት አስተማሪ ናቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ ተማሪዎች፡፡ አስተማሪው በክፍል ውስጥ ካሉት ተማሪዎች ውስጥ “አንቺ ሰማያዊ ቀሚስ የለበስሽው ልጅ፣ ስምሽ ማነው?” ሲሉ ጠየቋት፡፡

ልጅቱም ስሟን ተናገረች፡፡

አስተማሪው ከክፍሉ እንድትወጣ እና ሁለተኛም በእሳቸው የሕግ ትምህርት ክፍለ ጊዜ እንዳትገባ አስጠነቀቋት፡፡

ልጅቱ በጣም ግራ ተጋብታ ”ለምን? ምንስ አደረኩ?“ በማለት ጠየቀቻቸው፡፡

“ዳግመኛ ጥያቄ እንዳትጠይቂኝ፤ ግን ክፍሉን ለቅቀሽ ውጪ!” አሏት፡፡

ልጅቱ ግራ እየተጋባችም ቢኾን ከክፍሉ ወጣች፡፡ በክፍሉ ውስጥ የነበሩት የሕግ ትምህርት ተማሪዎችም እየኾነ ባለው ነገር ግራ ተጋቡ፡፡ አንዳቸውም ግን ምክንያቱን ለማወቅ አልጣሩም፡፡

አስተማሪው ልጅቱ ከወጣች በኋላ “ሕግ ለምን ያስፈልጋል? ለማንስ ነው የሚጠቅመው?” የሚሉ ጥያቄዎችን ለተማሪዎቹ አቀረቡ፡፡

“ለማኅበራዊ መስተጋብር፤ የሰዎችን መብት ለማስከበር እና ለማስጠበቅ፤ በመንግሥት ላይ እምነት እንድንጥል፤ ለፍትሕ…” የሚሉ መልሶች ከተማሪዎቹ ተሰጡ፡፡

አስተማሪውም “ለፍትሕ!” ያለውን ተማሪ ስለ መልሱ አመሥግነው “አሁን ጓደኛችሁ ላይ ያደረኩት ነገር ተገቢ ያልኾነ ነው አይደል?” ብለው ጠየቁና “አዎ ልክ አልሠራሁም፤ እናንተ ግን በድርጊቴ አልተቃወማችሁኝም፤ ለምን ከድርጊቴ ልታስቆሙኝ አልሞከራችሁም? ለምንስ ከኢ-ፍትሐዊነቴ አላስቆማችሁኝም?” ሲሉ ጠየቁ፡፡

አሁን ያስተማርኳችሁን ነገር በጥሞና ልትገነዘቡት ይገባል፡፡ እናንተ በኔ ድርጊት ምንም ያልተቃወማችሁት በእናንተ ላይ ምንም ነገር ስላልደረሰባችሁ ነው፡፡ ይህ አመለካከት ደግሞ ሁላችንንም ይጎዳናል፡፡ እኔን አይመለከተኝም፤ የኔ ጉዳይ አይደለም፤ ብላችሁ የምታስቡ ከኾነ ተሳስታችኋል፡፡

ማንም ፍትሕ እንዲሰፍን የሚፈልግ አካል በጓደኛችሁ ላይ የፈጸምኩትን ድርጊት ማውገዝ ነበረበት፡፡ ይህ ጉዳይ ‘ነግ በኔ’ እስከሚኾንባችሁ መጠበቅም አልነበረባችሁም፡፡

ፍትሕ እና እውነት ሁሌም እና በየትኛውም ቦታ መረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ለፍትሕ እና ለእውነት መታገልም የሁላችንም ድርሻ ነው፡፡

ብዙዎቻችን አብረን ብንኖርም አንዳችን ለአንዳችን ፍትሕ ስንታገል ግን አንታይም፡፡ ይህ የሚመነጨው ስለፍትሕ ካለመረዳት ሳይኾን ስለራሳችን ብቻ ስለምናስብ ነው፡፡ ለውስጣችን የምንነግረው እኔ ምንም ካልኾንኩ ‘ተመሥገን!’ ማለታችን ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ነገ በፍትሕ እጦት የሚበደለውን ተረኛ ሰው አናውቀውምና፡፡

በየጊዜው፣ በየትም ቦታና በማንኛውም ዘርፍ ኢ-ፍትሐዊነት ይፈጠራል፡፡ ይሄንን ችግር ለኾነ አካል ብቻ መተው ደግሞ ትክክል አይደለም፡፡ ፍትሕን ማስፈን ወይም እንዲሰፍን ማስቻል የሁላችንም ድርሻ ነው፡፡

ዛሬ ያስተማርኳችሁ እናንተም ኾናችሁ በዙሪያችሁ ያለው ማኅበረሰብ ፍትሕን ለማስፈን ድምጻችሁ ምን ያህል አቅም እንዳለው ነው፡፡ ስለ እውነት እና ስለ ፍትሕ ድምጹን ማሰማት ያለበት ተበዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ኹላችንም ከፍትሕ ጎን መቆም ይኖርብናል፡፡

ይህ በማኅበራዊ የትሥሥር ገጾች ሲዘዋወር የታየው የሕግ ትምህርት ለብዙዎቻችን ትምህርት እንደሚኾን አያጠራጥርም፡፡ ፍትሕን ማስፈን የመንግሥት ብቻ ሳይኾን የማኅበረሱም ድርሻ ነው፡፡

በቅርቡ የብዙ ኅብረተሰብ ክፍሎችን ልብ የነካው የሕጻን ሔቨን ጉዳይም የኹላችንንም ትኩረት የሳበው፣ ችግሩ የኹላችንንም ቤት ሊያንኳኳ የሚችል በመኾኑ ነው፡፡

በሰባት ዓመቷ ሕጻን ሔቨን ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት ተገቢ ፍትሕ ካልተሰጠው ጉዳቱ የእናቷ እና የሌሎች ዘመዶቿ ብቻ አይኾንም፡፡

የሔቨን ጉዳት የኹላችንም ጉዳት ነው፡፡ የሔቨን ጉዳት ለዓደባባይ የበቃ አረመኔያዊ ድርጊት ይሁን እንጂ ችግሩ የብዙ ኢትዮጵያዊያን ሔቨኖች ነው፡፡

ለሔቨን እና ለእናቷ ድምጽ መኾንም የፍትሕ ሥርዓቱን መጋፋት ሳይኾን ስለ ፍትሕ እና እውነት በየትኛውም ቦታ እና ዘርፍ ድምጽ መኾን ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”የውጭ የምንዛሬ ቢሮዎች ሲከፈቱ ሕጋዊ ሥርዓት ያለው እና ቀልጣፋ አገልግሎት ይኖራል” ቆስጠንጢኖስ በርኸ (ዶ.ር)
Next articleየሕጻን ሄቨን ጉዳይ የምርመራ፣ የክስ እና የፍርድ ሂደት እንዴት ነበር?