”የውጭ የምንዛሬ ቢሮዎች ሲከፈቱ ሕጋዊ ሥርዓት ያለው እና ቀልጣፋ አገልግሎት ይኖራል” ቆስጠንጢኖስ በርኸ (ዶ.ር)

97

ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚፈጥራቸው የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ እና የጥቁር ገበያን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ለማምጣት የሚያግዝ መኾኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርኸ (ዶ.ር) ይገልጻሉ።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ማግስት ጀምሮ በሁሉም ባንኮች ተግባራዊ የምንዛሬ ለውጥ ተደርጓል።

ማሻሻያውን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ከዚህ በፊት ያልነበሩ በአዲስ የሚፈጠሩ የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች የሚከፈቱ መኾናቸው ነው።

ብሔራዊ ባንክ ይፋ ባደረገው የውጭ ምንዛሬ ዳይሬክቲቭ መሠረት የምንዛሬ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ባንኮች እና ባንክ ያልኾኑ በአዲስ የሚቋቋሙ የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ናቸው።

አዲስ የሚከፈቱት ተቋማት የምንዛሬ አገልግሎት ላይ ብቻ ተሰማርተው ይሠራሉ። ኾኖም ቢሮዎቹን ከፍቶ ለመንቀሳቀስ የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላት እንደሚገባም የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ዳይሬክቲቭ ያስረዳል።

ከመስፈርቶች መካከል ቢሮውን ለመክፈት የሚቀርቡ አመልካቾች በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሊኾኑ እንደሚገባ ይገልጻል።

ሌላው ደግሞ ቢያንስ 15 ሚሊዮን ብር ካፒታል እና በጊዜ ገደብ በዝግ የሚቀመጥ 30 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል። በተጨማሪም የሚከፈቱ ቢሮዎች የሚኖራቸው የደኅንነት ጉዳይንም ከመስፈርቶች ውስጥ እናገኛቸዋለን።

ቀልጣፋ አገልግሎትን ከመስጠት፣ የጥቁር ገበያን ከማስቀረት እና ኢትዮጵያ በቂ የምንዛሬ መጠን እንድታገኝ ከማደረግ አንፃር አዲስ ይከፈታሉ የተባሉት የምንዛሬ ቢሮዎች የሚኖራቸውን ፋይዳ በተመለከተ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ቆስጠንጢኖስ በርኸ (ዶ.ር) ምን ይላሉ?

ሰዎች ከብዙ የዓለማችን ክፍሎች ሲመጡ ወይም ሲሄዱ ለተለያዩ አገልግሎቶች ምንዛሬን ሲፈልጉ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት መንገድ መኖር እንዳለበት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ይገልጻሉ። በተመሳሳይ ለጉብኝት እና ለተለያየ ዓላማ ወደ ሀገር የሚገቡ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች እና ዲያስፖራዎች በትላልቅ የገበያ ማዕከላት አካባቢ የምንዛሬ ችግር ሳይገጥማቸው በቅርብ የሚፈልጉትን ምንዛሬ ለማግኘት አማራጮች ቢኖሩ ቆይታን እና እርካታን ከመጨመር ባለፈ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታም ይኖረዋል።

እነዚህን እና ሌሎችንም ተግባራት ለማከናውን ታዲያ አዲስ ይከፈታሉ የተባሉ የምንዛሬ ቢሮዎች ተግባራዊ መኾን ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ዶክተር ቆስጠንጠኖስ በርኸ ጠቁመዋል።

እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያው ገለጻ የምንዛሬ ቢሮዎች መከፈት ተቋማቱ በምንዛሬ ላይ ብቻ ስለሚሰማሩ የተለያዩ ሀገራትን ገንዘብ የማቅረብ ዕድልን ከማስፋት ባለፈ ሕጋዊ የምንዛሬ ተቋማት ሲከፈቱ በቀላሉ ሄዶ ለመመንዘር አመቺ ስለሚኾን የጥቁር ገበያን በማዳከም ለማጥፋትም ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

አሁን ላይ በጥቁር ገበያ እና በባንኮች መካከል ያለው የምንዛሬ መጠን የተቀራረበ በመኾኑ ጥቁር ገበያ ላይ የተሰማሩ አካላት ወደ ሕጋዊ አሠራር እንዲገቡ የሚያበረታታ እና ተቋማቱ ሲከፈቱ ደግሞ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥሩ መኾኑን ባለሙያው ተናግረዋል።

በአዲሱ የምንዛሬ አሠራር ማሻሻያ ባንኮች የሚኖራቸው የዶላር መጠን ከፍ ስለሚል የጥቁር ገበያ በራሱ ጊዜ ወደ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲመጣ እና እንዲጠፋ የሚያስገድድ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋልም ሲሉ አክለዋል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው በአህጉራችን አፍሪካ ናይጄሪያ እና ኬንያ 30 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ከዳያስፖራ ቢያገኙም ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 800 ሚሊዮን ዶላር ብቻ አግኝታለች በማለት የዓለም ባንክ መረጃን ዋቢ አድርገው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ተናግረዋል።

በጥቁር ገበያ ወደ ሀገራችን የሚገባውን የውጭ ሀገር ገንዘብ ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ማምጣት ከተቻለ ኢትዮጵያ ከ12 እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ ማግኘት እንደምትችል እና እዳዋን በጥቂት ዓመታት ውስጥ መመለስ እንደሚያስችላት አስረድተዋል።

ከባንኮች ተጨማሪ የምንዛሬ ቢሮዎች ሲከፈቱ እና ከዲያስፖራ የሚገኘው የውጭ ሀገር ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ሲመነዘር በቂ ዶላር ይገኛል።

የጥቁር ገበያ የተፈጠረበት ዋነኛ ምክንያት የምንዛሬ እጥረትን ተከትሎ በመኾኑ በባንኮች እና በሚከፈቱ ተቋማት የሚገኘው የምንዛሬ መጠን ከፍ ሲል ጥቁር ገበያ የማይጠፋበት ምክንያት አይኖርም ሲሉም ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከኢኮኖሚ መረጋጋት እና ማገገም ወደ መመንጠቅ እድገት የመሸጋገር ሒደትን ያቀፈው የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ዘርፍ እቅድ ፍኖት ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ነው።
Next articleፍትህ ጠያቂ ድምጾች