
አዲስ አበባ: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የትውልድ ቁጭት ለትውልድ ልዕልና የማነፅ ትልም” በሚል መሪ ቃል የክልሉ መንግሥት የ25 ዓመት እቅድ አዘጋጅቶ ይፋ በማድረግ በየዘርፉ ውይይት እና ገለፃ እየተከናወነ ነው። የአማራ ክልል መንግሥት የአሻጋሪ እድገትና ዘላቂ ልማት ውስጥ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እቅድ በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላለሙ ባለሃብቶች ማብራሪያ የመስጠት እና ግብዓት የመውሰድ ምክክር እያደረገ ነው።
የዕቅዱ መሪ እና የኢኮኖሚ አማካሪው ሰኢድ ኑሩ (ዶ.ር) ግቡን ለማሳካት እቅዱ ታሳቢ ችግሮችን የለየ ሲኾን የድህነት ምጣኔ ከፍተኛ መኾን፣ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ንረት መኖር እንዲሁም ከፍተኛ የሥራ አጥነት ማለትም በክልሉ ካለው ወጣት የእድሜ ክልል አንድ አራተኛው ሥራ ፈላጊ መኾን ከግንዛቤ ገብቷል ብለዋል።
ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በሚደረገው ሽግግር ውስጥ ኢንዱስትሪው የሚፈለገውን ያህል ማደግ ሳይችል ቀርቶ እንደ ክልል ከጥቅል ኢኮኖሚው ውስጥ ሦስት በመቶ ብቻ ድርሻ ያለው በመኾኑ ልዩ እቅድ መሥራት ማስፈለጉን ዶክተር ሰኢድ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከዓለም ሀገራት ጋር ስትነፃፀር አንደ ሀገር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ናት። አማራ ክልል ደግሞ ከሀገሪቱ አካባቢዎች ሲነፃፀር ከኦሮሚያ እና ከአዲስ አበባ አንፃር በከፍተኛ ርቀት ዝቅ ያለ ነው።
ይህ የኢንዱስትራላይዜሽን እቅድ በ2027 ኢንዱስትሪ የራሱን ፍላጎት የሸፈነ ትክክለኛ የእድገት እና ብልፅግና ፍኖትን የያዘ መኾኑን ያረጋገጠ እንዲኾን ማድረግ ነው። በ2042 ደግሞ የአማራ ክልል በዓለም ተወዳዳሪ በመኾን የዘመናዊ ኢኮኖሚ ባለቤት ኾኖ ማየት ዋና ግቡ ነው።
የ25 ዓመት እቅዱ የኢንዱስትሪ እቅድ ትልም ሦስት ደረጃዎች አሉት። የኢኮኖሚ መረጋጋት እና ማገገም፣ የመመንጠቅ ደረጃ እና የመበልፀግ ደረጃዎችን የያዘ ስለመኾኑ ዶክተር ሰኢድ አብራርተዋል።
ይህንን ለማሳካት ቴክኖሎጂውን ማሻሻል፣ መኮረጅ፣ ማስገባት እና መፍጠር አስፈላጊ መኾኑን የእቅዱ ማሳኪያ መንገድ ተድርጎ ተመላክቷል።
ምግብ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ቆዳ፣ መድኃኒት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ ኬሚካል እና ብረታ ብረት በየደረጃዎቹ እቅዱ ትኩረት ያደረገባቸው ምርቶች መኾናቸው ተነግሯል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!