ሰቆጣ ለሻደይ በዓል የሚገቡ እንግዶቿን በፍቅር እና በክብር እየተቀበለች ነው።

120

ሰቆጣ: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰቆጣ ከተማ ለሻደይ በዓል ወደ ከተማዋ የሚገቡ እንግዶችን በመቀበል ላይ እንደምትገኝ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላሽ ወርቃለም ገለጹ፡፡

ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሰቆጣ ከተማ የሚከበረውን የሻደይ በዓልን በማስመልከት የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላሽ ወርቃለም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላሽ “ሻደይ የዋግ ኽምራ መገለጫ የሴቶች የነጻነታቸው ማረጋገጫ በዓል ነው” ብለዋል።

የሻደይ በዓልን ለማክበር ባሕላዊ ትውፊቱን፣ ወጉን እና እሴቱን በጠበቀ መልኩ በዋግ ሹሞች መናገሻ በሰቆጣ ከተማ በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ስለማጠናቀቃቸው ነው ያስረዱት፡፡ አቶ መላሽ ሰቆጣ ከተማ እንግዶችን በመቀበል ላይ እንደምትገኝም ነው ያብራሩት።

የሻደይ በዓል የማኅበረሰቡ የመጠያየቂያ እና የመገናኛ በዓልም ጭምር ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላሽ ሻደይ በዋግ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ማኅበራዊ መስተጋብር የሚፈጥር ተወዳጅ በዓል ነው ብለዋል።

የሻደይ በዓልን ለማክበር ወደ ሰቆጣ ከተማ ለመጡ የባሕል ተጫዋቾች፣ እንግዶች እና ተሳታፊዎች በሰላም በዓሉን ማክበር የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሥራው ቀድሞ ስለመጠናቁ ነው ያስገነዘቡት።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላሽ ወርቃለም የሻደይ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የመተሳሰብ በዓል እንዲኾንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዘር የተሸፈኑ ማሳዎችን ከበሽታ እና ከተባይ ለመታደግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል” የክልሉ ግብርና ቢሮ
Next articleከኢኮኖሚ መረጋጋት እና ማገገም ወደ መመንጠቅ እድገት የመሸጋገር ሒደትን ያቀፈው የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ዘርፍ እቅድ ፍኖት ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ነው።