“በዘር የተሸፈኑ ማሳዎችን ከበሽታ እና ከተባይ ለመታደግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል” የክልሉ ግብርና ቢሮ

56

ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አቶ ሙላት ዓለማየሁ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ወረብ ቆላ ጺዮን ቀበሌ ቤዛዊት ቀጣና የሚኖሩ አርሶ አደር ናቸው፡፡

አርሶ አደር ሙላት 1 ነጥብ 5 ቃዳ መሬት በመስኖ በማልማት እስከ 12 ኩንታል ማዳበሪያ የስንዴ ምርት ለመሠብሠብ እንዳቀዱ ይናገራሉ፡፡

አርሶ አደሩ ከአረም፣ ከተባይ እና ከበሽታ ነጻ የኾነ ምርት ለማምረት ማሳቸውን ደጋግመው እንዳረሱ እና ምርጥ ዘር መርጠው እንደተጠቀሙ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ከአየር ንብረቱ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል ከግብርና ባለሙያ ጋር በመነጋገር በቡቃያው የመድኃኒት እርጭት እንደሚከውኑም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በ2016/2017 የምርት ዘመን 5 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል፡፡

ይህንን ምርት ከአረም እና ከተባይ ነጻ በማድረግ የተሻለ ምርት ለመሠብሠብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለበት የክልሉ ግብርና ቢሮ የእጽዋት ጥበቃ ባለሙያ አሻግሬ እንዳየ ተናግረዋል፡፡

ዘር ዘርቶ ምርት ማፈስ እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ አይደለም የሚሉት ባለሙያው የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘት በሰብሉ ላይ የሚነሳን ተባይ መከታተል እና አረም ማረም ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ባለሙያው እነዚህን ክስተቶች በትክክለኛው መንገድ እና በሰዓቱ መከወን ካልተቻለ ምርቱን ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋው እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ የዕጽዋት ጥበቃ ሥራዎችን በቅንጅት ከአርሶ አደሩ ጋር መሥራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

አቶ አሻግሬ ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የኮሞዲቲ ሥራ በመሥራት፣ ቁጥጥር በማድረግ፣ በሰፊ ማሳ ላይ አንድ ዓይነት ሰብልን እንዲዘሩ በማድረግ፣ የዕጽዋት ጥበቃ ሥራዎችን በመሥራት ምርቱን ከተባይ በመከላከል እና የአረም ቁጥጥርን በጋራ በመሥራት የተሻለ ምርት ለመሠብሠብ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

አረምም ኾነ ተባዮች በጥራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ስለሚያደርሱ ምርቱ በገበያም ኾነ በተጠቃሚው ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጸዋል፡፡

አቶ አሻግሬ እንዳሉት አርሶ አደሩ ማሳውን በየጊዜው ማሰስ አለበት፣ ተባይ ወይም በሽታ ከተከሰተ የበሽታው የተባዩን ዓይነት እና መጠን፣ ከሰብሉ ላይ ያሳረፈውን ችግር እና የመከላከል ሥራው ምን መኾን አለበት የሚለውን ከባለሙያ ጋር በመለየት የተቀናጀ የተባይ እና የበሽታ መከላከል ሥራዎች መሥራት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው በሰፊ ማሳ ላይ ቢጫ ዋግ ቢከሰት እና አንድ ጊዜ ሰብሉን የሚያጠፋው ኾኖ ቢገኝ በባለሙያ በመታገዝ የኬሚካል እርጭት መደረግ እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሩ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ አረምን በመንቀል፣ ደጋግሞ በማረስ፣ አካባቢውን ንጹህ በማድረግ፣ ጥሩ ዘርን በመምረጥ፣ ከዘር ጋር የሚመጡ አረሞችን ቀድሞ በመለየት፣ ብቅለቱን በመከታተል ሰብሉን ከበሽታ፣ ከተባይ እና ከአረም ሊከላከል ይገባል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየ”ኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ሐሳብ የንግድ ኢግዚቢሽን ሳምንት ሊካሄድ ነው።
Next articleሰቆጣ ለሻደይ በዓል የሚገቡ እንግዶቿን በፍቅር እና በክብር እየተቀበለች ነው።