
አዲስ አበባ: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ከነሐሴ 19 እስከ 23/2016 ዓ.ም ድረስ “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ሃሳብ የንግድ ኢግዚቢሽን ሳምንት ሊያካሂድ እንደኾነ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
መግለጫውን የሰጡት ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የሀገር ውስጥ ንግድን በማዘመን የምርትና የንግድ ዝውውሩን ቀልጣፋ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶቾ ጥራታቸውን አሟልተው የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ ለማስቻልም እየተሠራ እንደኾነ አንስተዋል።
በዚህም መሠረት አንድም የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በሌላ በኩል ደግሞ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እና ተወዳዳሪ ለመኾን በመጪው እሁድ ነሀሴ 19 “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ሃሳብ የንግድ ኢግዚብሽን እንደሚካሄድ አንስተዋል።
የንግድ ኢግዚቢሽኑ የሚካሄደው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ እንደኾነ ያነሱት ሚኒስትሩ በኢግዚብሽኑ የቡና ምርቶች፣ የቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች፣ ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ የከበሩ ማዕድናት፣ ስጋ እና የስጋ ውጤቶች፣ የቅባት እህሎች፣ ጫት እና ሌሎች የሀገር ውስጥ ምርቶች በምስል እና በቪድዮ ቀርበው ሻጭና ገዢዎች ስምምነት የሚያደርጉበት ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም ኅብረተሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የሰንበት ገበያዎች በኢግዚብሽኑ እንደሚሳተፉ እና ነዋሪው በዝቅተኛ ዋጋ የሚፈልገውን ምርት የሚገበያይበት መድረክም መኾኑን አንስተዋል።
የንግድ ኢግዚብሽን ሳምንቱ በተለያዩ ሚኒስትር ተቋማት እና በኅብረተሰቡ እንደሚጎበኝ የገለፁ ሲኾን በሳምንቱ የተለያዩ መሰናዶዎች እንደሚኖሩም ሚኒስትሩ ዶክተር ካሳሁን በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
የንግድ እና የግሉ ዘርፍ አሉኝ የሚሏቸውን ጥያቄዎች ይዘው ለመንግሥት የሚያቀርቡበት እና የሚወያዩበት መድረክ እንደሚካሄድም አንስተዋል።
የሀገር ውስጥ እና የሀገር ውጭ ንግዶች ላይ ትኩረት ያደረጉ የፓናል ውይይቶች እንዲሁም የሽልማት እና የእውቅና ፕሮግራምም ይኖራል።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!