
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም የወረዳ እና የከተማ አሥተዳደር መሪዎች የተሳተፉበት የደቡብ ጎንደር ዞን የመንግሥት እና የድርጅት፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ግምገማዊ መድረክ ተከናውኗል።
በመድረኩ የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ተገምግሟል።
ዕቅዶችን ወደተግባር የሚተረጉሙ ጠንካራ መሪዎችን በመፍጠር እና ለሕዝብ በመሥራት ልማትን ማፋጠን እንደሚገባ በመድረኩ ላይ ተነስቷል።
የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ሊጠናቀቁ ባለመቻላቸው የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ መነሻ ኾነዋል፤ የፌዴራል መንግሥት ጭምር ጉዳዩን ወስዶ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ መሥራት እንዳለበት በመድረኩ ተነስቷል።
የወረዳውን ዕቅድ ለመፈጸም መሪዎች ቁርጠኛ መኾን እንዳለባቸውም ተጠቁሟል። ለዚህም ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መዘርጋት እንዳለበት ተነስቷል። ተግባር እና ኀላፊነቱን በማይወጣ አካል ላይ የተጠያቂነት ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባም ተጠቁሟል። የእርምት ሂደት መተግበር እንደሚገባም ነው የተመላከተው።
ያለፈውን የ2016 በጀት ዓመት በመፈተሽ፤ የ2017 ዓ.ም ዕቅድን ለመፈጸም የመሪዎች ቁርጠኝነት እና ቁመና ሲፈተሽ ዞኑ፣ ወረዳው እና ከተማ አሥተዳደሩ ምን ላይ ነው ያለው በሚለው ጉዳይም አጽንኦት በመስጠት አንኳር አጀንዳዎች ተነስተው መፍትሔ ተቀምጧል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የደራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ እስቲበል ጓዴ ሰላም እና ልማት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ብለዋል፡፡
አቶ እስቲበል ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን ማልማት እና ሕዝቡ በልቶ እንዲያድር ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ልማትን ዋና አጀንዳ አድርጎ መሥራት ካልተቻለ ግጭትን በዘላቂነት መፍታት እንደሚያዳግትም ጠቁመዋል።
በ2016 ዓ.ም ከመንግሥት አኳያ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተወሰደው ቁርጠኝነት እና የተደረገው የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም ስርጭት ማኅበረሰቡ ለመንግሥት ያለው ምልከታ መልካም እንዲኾን አስችሏልም ብለዋል።
መሪዎች ተናባቢ እና ገቢራዊ ሊኾን የሚችል ዕቅድ በማዘጋጀት እንዲሁም ሕዝብን በማሳተፍ መፈጸም እና አገልጋይ ብቻ መኾናቸውን ዐውቀው የሚመሩ መኾን እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ዞኑ በሚሠራቸው የሰላም ግንባታ እና የልማት ሥራዎች አመራር ሰጭነቱ እና የተግባር አፈጻጸሙ ለሌሎች ዞኖችም ተምሳሌት ነው ብለዋል።
የከተሞች እና ገጠር ወረዳ ወሰን ማካለል ተግባራት ላይ የተፈጥሮ ሃብት የኾነውን የመሬት ሃብት መጠበቅ እና የተናበበ ሥራ መሠራት እንዳለበትም አሳስበዋል። ከተሞችን ለማልማት የአመራር ሰጭነት ሚናን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ እንደሚያመላክተው “መሪ ሲኮን ቀውስን በመቀልበስ ሕዝብን ለማሻገር፣ ችግርን ለመፍታት፣ በፈተና ሂደት ውስጥ በማለፍ ሕዝብንም ተጠቃሚ ለማድረግ መሥራት ይጠይቃል” ሲሉም ተናግረዋል።
የክረምት የግብርና፣ የገቢ እና የማኅበራዊ ሥራዎች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የቁጭት ተስፋ የሰነቀ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት ይጠይቃል ብለዋል አቶ ሲሳይ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!