
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ዕቅድ አፈጻጸም ተገምግሟል።
በዕቅድ አፈጻጸም ግምገማው የተሳተፉ የሥራ ኀላፊዎች በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባር ለአቅመ ደካሞች እና አዛውንቶች ቤት ለቤት የነጻ ሕክምና ለመስጠት አቅዶ ከመሥራት አንጻር መሻሻል የታየበት ነው ብለዋል።
የክረምት ወቅት ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ትምህርት ቤቶችን የማደስ እና ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት ላይ በከተማ እና በገጠር ወረዳዎች በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰለሞን ይትባረክ በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ400 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ከ130 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ የበጎ ፈቃድ ተግባር ከህሊና እረፍት አልፎ በፈጣሪ ዘንድም ተወዳጅ ተግባር በመኾኑ በተለይ ወጣቱ በትኩረት ሊሳተፍ እንደሚገባ አስረድተዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ለማሳካት የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ በየደረጃው ያሉ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ በችግኝ ተከላ፣ ማዕድ በማጋራት እና በሌሎችም በርካታ ዘርፎች እየተካሄደ ይገኛል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!