
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ዓመት በዓላት ሲመጡ ከበዓል ጋር ተያየዘው ገበያዎችም ሞቅ ሞቅ ይላሉ። የሰቆጣ ከተማው ማክሰኞ ገበያም የሻደይ በዓል መድረስን ተከትሎ እንደወትሮው በሙክት፣ በበግ እና በፍየል ሳይኾን በመዋቢያ ጌጦች እና በአልባሳት ተሞልቷል።
ከገጠርም ከከተማም የመጡ ሸማቾችም ለሻደይ ያስፈልገናል ያሉትን እየሸመቱ ይውላሉ።
እኛም በቦታው ተገኝተን ገብያ አንዴት ነው? ብለን ተየቅን።
የዘንድሮው ገበያ ከአምና የጨመረ መኾኑን ሸማቾች ይናገራሉ። የአንባር እና የድኮት ጌጣጌጦችን ለመሸመት የመጣችው እለኒ ደሴ ለሻደይ አምራ እና ተውባ ለመገኘት ማክሰኞ ገበያ ተገኝታለች። የዘንድሮው የጌጣጌጥ ገበያ ከባለፉት ዓመታት በመጠንም ይሁን በዓይነት ስለመጨመሩ ገልጻለች።
“ለሻደይ ያልኾነ ሽኳርና ድኮት
ለሻደይ ካልኾነ ብል ይብላው” አታውጡት እንዲሉ አበው የሻደይ በዓልን በድምቀት ለማክበር መዘጋጀቷን እለኒ ተናግራለች።
የሻደይ በዓልን ተከትሎ ገበያው የሚደምቀው በባሕል አልባሳቱ ሲኾን ወይዘሮ ቃል ኪዳን ጌታው መቀነት ለመሸመት ማክሰኞ ገበያ መገኘታቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል።
በልጃገረዶች መድመቂያ እና መዋቢያ በኾነው የሻደይ በዓል አምሮ እና ደምቆ ለመዋል ዝግጅት ስለማድረጋቸውም ነው የገለጹት።
የጌጣጌጥ እቃዎች ላይ አንጻራዊ የዋጋ ጭማሪ ስለመኖሩ የጌጣጌጥ ነጋዴው ዲያቆን አሰፋ ነጋሽ ተናግረዋል።
የዋግ ኽምራን ባሕል የሚያሳዩ ጌጣጌጦችን መሠረት አድርገው ለተጠቃሚ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መኾኑንም ገልጸዋል።
በባሕል አልባሳት ላይ የተጋነነ ጭማሪ እንደሌለው እና ለሻደይ በዓል የሚኾን አልባሳት ለተጠቃሚ በስፋት እያቀረቡ መኾኑን የባሕል አልባሳት ነጋዴዋ ወይዘሮ ዘሐራ መሐመድ ተናግረዋል።
በሻደይ ባሕላዊ አልባሳት ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ አለመኖሩን የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙላት አመረም ተስማምተውበታል።
በዓሉን ተከትሎ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከመቆጣጠር ባለፈ ከሚመለከተው አካል ጋር በቅርበት በመነጋገር ገበያ የማረጋጋት ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ኀላፊው የዋግ ኽምራ መገለጫ ለኾነው እና ለልጃገረዶች የነጻነት ቀን ለኾነው ለሻደይ በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!