
አዲስ አበባ: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ከከተማው የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በጋራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂዷል።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ ባልቻ በከተማ ደረጃ 20 ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።
ኀላፊው ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ልማት በተሠራው ሥራ 2 ነጥብ 8 የነበረውን የከተማዋን የደን ሽፋን ወደ 17 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሣቢ ሙሉጌታ አበበ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር እና ሕዝብ ጥቅም በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸው ችግኝ ከመትከል ጎን ለጎን ሰው ተኮር ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ዓለማየሁ ሚጀና በክፍለ ከተማው 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ችግኞችን በዘንድሮው ዓመት ለመትከል መታቀዱን አንስተዋል።
እስካሁንም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን ገልጸው የሚተከሉ ችግኞችን የጽድቀት ምጣኔ ለማሳደግ የተተከሉትን መንከባከብ ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚበዙበት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከኢንዱስትሪ የሚወጡ ብክለቶችን ለመከላከል የአረንጓዴ ልማት ላይ በተለየ ሁኔታ እየተሠራ መኾኑ የተገለጸ ሲኾን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩም በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተካሂዷል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!