
ባሕር ዳር: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወባ መከላከል ሥራዎችን ለማጠናከር ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚገመት የፀረ ወባ መድኃኒቶች በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚሰራጩ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) የኢትዮጵያ ልዑክ ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር ከተመራ ልዑካን ቡድን ጋር የወባ መከላከያ አጎበር ግዢ በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።
በየጊዜው ዋጋው እየጨመረ የመጣውን አጎበር በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረት እንደሚረግም ዶክተር መቅደስ ገልጸዋል።
መንግሥት እየተገበረ በሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ የሕክምና ምርቶች አምራቾችን ወደ ሀገር ለመሳብ ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው ከድርጅቶቹ ጋር በአጋርነት እየተሠራ መኾኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በስርጭት ላይ የሚገኘው አጎበርና የወባ መድኃኒት በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉና በተፈለገው ቦታ ተደራሽ መኾኑን ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) የኢትዮጵያ ልዑክ ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የወባ መከላከያ መድኃኒት የበሽታው ስርጭት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች እንደሚሰራጭ ገልጸዋል።
ድርጅቱ የወባ መድኃኒት ተደራሽነትን ለማሳደግ እንደሚሠራና በኢትዮጵያ የወባ መከላከል ሥራዎችን መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
በሀገር ውስጥ የወባ መድኃኒቶችን ለማምረት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ መናገራቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) የኢትዮጵያ ልዑክ ዳይሬክተር ስኮት ሆክላንደር የተመራው ልዑካን ቡድን ትናንት ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ.ር) ጋር መወያየቱ ይታወቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!