
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ከረፋዱ ጀምሮ ሥራ አቁሙ ተብሏል በሚል ውዥንብር ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል። በዚያው ዕለት ከሰዓት በኋላም የክልሉ እና የከተማው የመንግሥት አካላት እና የጸጥታ ኀይሉ ምንም ችግር እንደሌለ አስታውቀዋል።
በማግሥቱ ቅዳሜም ሕዝብ የተሰራጨው ስጋት ትክክል አለመኾኑን ሲገነዘብ ወደ መደበኛ ሥራው መውጣት ጀምሯል።
እሁድ የእረፍት ቀን ስለኾነ መሥሪያ ቤቶች ባይከፈቱም ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ድርጅቶች እና ኅብረተሰቡ በተሻለ ሁኔታ ሲንቀሳቀሱ እና ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን በሰላም ሲከውኑ መዋላቸው ተስተውሏል።
የባሕር ዳር የዛሬ ውሎም ካለፉት ቀናት የበለጠ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ያለ ስጋት በነጻነት ሲከወኑባት ነው የዋለው።
እንደተለመደው ጊዮርጊስ እና ፓፒረስን መነሻ እና መድረሻ ያደረጉ የእግረኛ እና የታክሲ እንቅስቃሴዎች መደበኛ ኾነው ውለዋል። ከሆስፒታል፣ ከካቶሊክ እና ከገጠር መንገድ፣ ከአሥራ ስድስት፣ ከልደታ፣ ከአዲሱ መነኻሪያ፣ ከፔዳ፣ ከቴክስታይል እና ከዓባይ ማዶ
ነዋሪዎች ጉዳያቸውን በሰላም ሲፈጽሙ ውለዋል።
ጫማ አሳማሪዎች፣ የጀበና ቡናዎች፣ ሱቆች፣ ባንኮች፣ እና ሌሎችም አምራች እና አገልግሎት ሰጪዎች እንደ ወትሮው ሁሉ አገልግሎታቸውን በሰላም ሲሰጡ ውለዋል። መሥሪያ ቤቶች እንደ ሁልጊዜው ሥራቸውን ሲከዉኑ መዋላቸው ታይቷል።
የአየር መንገድ ታክሲዎች የተለመደ አገልግሎት እየሰጡ ነው። ዕለቱ ደመናማ እና ዝናባማ በመኾኑ እንደ ልብ ካለማንቀሳቀሱ በስተቀር ጉዳይ ኖሮት በስጋት ያልወጣ ሰው ያለ አይመስለኝም ነው ያለችን በጀበና ቡና የምትተዳደር ወጣት።
ወጣቷ ሥራ ይቁም ስለተባለው ክልከላ ስትናገር ”ከዚሁ አነስተኛ ሥራየ ብሶ አትንቀሳቀሱ ከተባለ ምን ሠርቼ ልበላ ነው?” ስትልም ትጠይቃለች። ወጣቷ አለመሥራት ችግራችን ይፈታዋል ወይ ስትልም ትጠይቃለች።
ታላቅ ወንድሟ በድንገተኛ አደጋ ሆስፒታል የገባባት ሴት ደግሞ የከተማው ሰላም ጥሩ በመኾኑ ተራውጣ መድኃኒት መግዛት መቻሏን ነው የነገረችን። እንደተወራው ሰላም ባይኾን ምን ይውጠኝ ነበር ስትልም የሰላምን አስፈላጊነት ታሰምርበታለች።
በተለምዶ ዓባይ ማዶ በመባል የሚጠራው የከተማዋ ክፍልም ሰላም መኾኑን እና የእለት ከእለት እንቅስቃሴዎች በሰላም ሲከወኑ መዋሉን ነው ነዋሪዎች የገለጹት።
ሥራ እንዴት ነው ያልነው የታክሲ ረዳት ”ከሰዓት በፊት ብራ በመኾኑ ጥሩ ስንሠራ ውለናል፤ ከሰዓት በኋላ ግን ካፊያ በመኾኑ ብዙ መጥራት ግድ ብሎናል” ነው ያለው።
የአማራን ሕዝብ ጥያቄ እና ችግር ለመፍታት ሥራ ማቆም እና እንቅስቃሴ መገደብ በድህነት ላይ ድህነት መጨመር ካልኾነ በስተቀር መፍትሔ እንደማይኾን ነው አስተያየት ሰጪዎች የሚናገሩት።
በሥራ አጥነት እና በኑሮ ውድነት የሚሰቃይን ሕዝብ ‘አትሥራ፤ ቤት ዘግተህ ዋል’ ማለት በረሀብ ሙት ማለት መኾኑን ነው የሚገልጹት። ”ሥራ በማቆም ለዕለት ድሃውን፤ በዘላቂውም የክልሉን ምጣኔ ሃብት ከመጉዳት ውጪ ምን ተጽዕኖ ይፈጥራል? ለአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችስ ምን መፍትሔ ያመጣል?” ሲሉም ይጠይቃሉ።
የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች በሰላማዊ ንግግር እና ድርድር ለመፍታት የሚቻልበት አማራጭ መንግሥት አቅርቧል። ይህንን ዕድል መጠቀም ያለበት ተዋጊ ኀይሎች ብቻ ሳይኾኑ ሕዝቡ ጭምር ነው ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።
አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን የተደላደለ ኑሮ እየኖሩ፤ ልጆቻቸውን በክረምቱ የማጠናከሪያ ትምህርት እያስተማሩ፤ ሌሎች ምስኪኖች ግን ማለቂያ በሌለው እና አሸናፊው በማይለይበት የወንድማማቾች ጦርነት እንዲሞቱ ይገፋፋሉ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎች። ይህ ደግሞ የሰላም እጦታችን አባብሶ ወደማንወጣው አዘቅት ያስገባን ካልኾነ በስተቀር ለአማራ ሕዝብ ጥያቄም መፍትሔ አያመጣም ነው ያሉት።
በኀላፊነት ቦታ የሚገኙ እና አገልግሎት የሚጠበቅባቸው አንዳንድ አካላትም መፍትሔ ከመኾን ይልቅ ችግር ፈጣሪ ሲኾኑ አስተውለናል።
በአጠቃላይ ባሕር ዳር ከቅዝቃዜ እና ዝናባማ የዓየር ንብረቷ በስተቀር ዛሬም ሰላማዊ እና ጤናማ የኅብረተሰብ መስተጋብር ስታስተናግድ ውላለች።
የከተማው ሕዝብ ግድ እየኾነበት እና ስጋት እየገባው እንጂ ሥራ ማቆምን እንዳልፈለገው ነው መረዳት የሚቻለው። “ወደቀ ሲባሉ ተሰበረ” የሚሉትን ጨምሮ ግርግሩ ይጠቅመናል ብለው የሚያስቡ በሚያስወሩት ወሬ መሸበሩ ቢቆም ምኞታቸው እንደኾነ ነው ነዋሪዎች የገለጹት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!