
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረታቦር በዓል በታሪካዊቷ ደብረታቦር ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል፡፡
በዓሉ በርእሰ አድባራት ደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በሚያዘው አግባብ ተከብሯል፡፡
የደብረታቦር (የቡሄ) በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በየዓመቱ ነሐሴ 13 የሚከበር በዓል ሲኾን በደብረታቦር ከተማ በዓሉ በርእሰ አድባራት ደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በሚያዘው አግባብ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡
የደብረታቦር ደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት ምስክር መምህር መምህረ መምህራን በጽሀ አለሙ ላቀው እንደገለጹት ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን እና ክብረ መንግሥቱን ለሐዋርያቱ መግለጡን በማሰብ የደብረታቦር (የቡሄ) በዓል በየዓመቱ ነሐሴ 13 እንደሚከበር አስረድተዋል፡፡
የደብረታቦር በዓልን በደብረታቦር ማክበር የተለየ ስሜትን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
በዓሉን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው አግባብ በማክበር እና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
መምህረ መምህራን በጽሀ አለሙ የደብረታቦር በዓል የፍቅር እና የመተሳሰብ በዓል በመኾኑ በዓሉን በፍቅር እና በመተሳሰብ ማክበር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው አንዱ ለሌላው በማሰብ እና በመተጋገዝ መከበር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
በርእሰ አድባራት ደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን የደብረታቦር (የቡሄ) በዓልን ያከበረው ወጣት ታምሩ አወቀ ከጓደኞቹ ጋር በመኾን ደስ ብሎት በዓሉን በጨዋታ እና በሌሎችም ሁነቶች ማክበራቸውን ተናግሯል።
አንዳንድ ወጣቶች ባሕላቸውን በደንብ ከማወቅ ይልቅ ዘመናዊነቱ የሚያጠቃቸው መኾኑን ጠቁሞ ለባሕል ትኩረት ቢሰጥ ሲል ተናግሯል።
የደብረታቦር (የቡሄ) በዓል ከሃይማኖታዊ አከባበሩ በተጨማሪ በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር በፓናል ውይይት እና በሌሎችም ዝግጅቶች ተከብሯል።
የበዓሉን አከባበር ከአሁኑ በበለጠ ለማስኬድም ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል በባለቤትነት ይዞ ሊሠራ እንደሚገባ ከደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!