
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከሰሞኑ በአማራ ክልል ታላላቅ ከተሞች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ለማድረግ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚመላለሱ ሐሰተኛ መረጃዎች ይታያሉ።
ከቀናት በፊት በክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር እንቅስቃሴ እንዲቆም ተብሏል በሚል በተሠራጨው መረጃ ምክንያት ለግማሽ ቀን የሚኾን የከተማዋ እንቅስቃሴ ተገትቶ ነበር።
በከተማዋ ያለው የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ የተረጋገጠ መኾኑን የጸጥታ ኀይሉ በማስታወቁ መደበኛ እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት ተመልሷል።
በሌሎች የክልሉ ከተሞችም መደበኛ እንቅስቃሴ እንዳይኖር የሚፈልጉ መረጃዎች ሲወጡ ይስተዋላሉ።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውበሸት በከተማዋ መደበኛ የሕዝብ እንቅስቃሴ እና ሥራዎች መቀጠላቸውን ተናግረዋል። በከተማዋ የቡሔ በዓል መከበሩንም ገልፀዋል። በታላላቅ ከተሞች ላይ የሚነዛው አሉባልታ በሕዝብ ዘንድ ተጽዕኖ እንዳያሳድር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የጸጥታ መዋቅሩ አስፈላጊውን ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ እና በከተማ የሰላም እና የጸጥታ ችግር አለመኖሩን አመላክተዋል። ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው ያስታወቁት።
የከተማዋ ነዋሪዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ፍላጎታቸውን እየገለጹ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ፍላጎት ብቻ ሳይኾን በተግባርም እያሳዩ ያሉት ሰላም ወዳድነታቸውን ነው ብለዋል።
በከተማዋ መደበኛ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በመደበኛነት ቀጥለዋል ነው ያሉት። በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚዘዋወሩ ሐሰተኛ መረጃዎች መኖራቸውን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የከተማዋን ሰላም በተመለከተ የሚዘዋወረው መረጃ ፈጽሞ ስህተት ነው ብለዋል። ከተማ ውስጥ የተስተጓጐለ የትራንስፖርት እንቅስቃሴም ኾነ የቆመ አገልግሎት የለም ነው ያሉት።
ደብረ ብርሃን የኢንዱስትሪ ከተማ ናት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የከተማዋ ሰላም በጥሩ ሁኔታ መቀጠል የኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ጥሩ እንዲኾን ማድረጉን ነው የተናገሩት። ሰላምን ማስቀጠል የኅብረሰቡን የልማት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል፣ ሁሉም አካል ለሰላም የድርሻውን መወጣት ይገባዋል ብለዋል።
የከተማ እድገት እና የነዋሪዎች የኑሮ ሁኔታ የሚሻሻለው ሰላም ሲኖር ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለሰላም ዘብ መቆም አለበት ነው ያሉት። ባለፉት ዓመታት በከተማዋ ሰላም በመኖሩ መሠረታዊ የከተማ እድገት መታየቱንም ተናግረዋል። የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል የከተማዋን እድገት ውጤታማ እንደሚያድርገውም አስታውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!