
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደብረ ታቦር (የቡሄ) በዓል በኮምቦልቻ ከተማ መድሐኒዓለም ቤተክስቲያን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ተከብሯል፡፡
የደብረ ታቦር በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት እና ድምጸ መለኮቱ የተሰማበትን ጊዜ ለማሰብ እንደሚከበር የመድሐነዓለም ቤተክስቲያን አሥተዳዳሪ መላዕከ ሰላም ቆሞስ አባ ሳሙኤል ወልደ ገብርኤል ገልጸዋል።
ሰዎች ከጭጋጋማው የክረምት ጊዜ ወደ ብርሃኑ ጊዜ መሸጋገራቸውን ለመግለጽ በሚከውኑት ትውፊታዊ ሥነ ሥርዓት በዓሉ ደምቆ እንደሚከበርም ነው የተናገሩት። በዓሉ በሃይማኖታዊ እና በባሕላዊ ክዋኔዎች እንደሚከበርም አስገንዝበዋል።
በዓሉ ሲከበር ለሰው ልጆች “ሰላም” አስፈላጊ እና መሠረታዊ ጉዳይ በመኾኑ ሰላም እንዲሰፍን በመጸለይ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ እንዲኾንም መላዕከ ሰላም ቆሞስ አባ ሳሙኤል ወልደ ገብርኤል መልዕክት አስተላልፈዋል።
የደብረ ታቦር በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበር ሲኾን በኮምቦልቻ ከተማም በመድሐኒዓለም ቤተክስቲያን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በሚያዘው መሠረት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ የባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈትለወርቅ መሀመድ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከኮምቦልቻ ከተማ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!