“የፍትሕ ሥርዓቱን አገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ ተቋማቱን በቴክኖሎጂ ማጠናከር ይገባል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

17

ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አሠራሩን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ከክልሉ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን እና ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ሥምምነት አድርጓል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው እንዳሉት የዳኝነት አገልግሎቱን ፈጣን እና ወጭ ቆጣቢ ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት የማሻሻያ ሥራዎችን ሢሠራ ቆይቷል። አሁን ላይም ተቋሙ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና በአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ሥምምነት ላይ ብለዋል።

በኤሌክትሮኒክስ አሠራር በመዘርጋት ተገልጋዮች ባሉበት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚያግዝ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። ይህም ፋይል ለማስከፈት ከቦታ ቦታ የሚደረግን ጉዞ ያስቀራል ነው ያሉት።

የድምጽ ክርክሮችን ወዲያውኑ ወደ ጹሑፍ በመቀየር የውሳኔ ግልባጭ እንዲያገኙ እና ተገልጋዮች ጉዳያቸውን ለመከታተል ከቦታ ቦታ መሔድ ሳያስፈልግ በሞባይል በሚጫን አፕሊኬሽን ላይ የመዝገብ ቁጥርን በማስገባት አገልግሎት የሚያገኙበት አማራጮች ለመተግበር ያግዛል ተብሏል።

የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የቻለ ይግዛው እንዳሉት የክልሉን ፍላጎት መሸከም የሚችል የቴክኖሎጂ ተቋም መገንባት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል። የሚሠሩ ቴክኖሎጂዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ ቴክኖሎጂውን መጠቀም የሚችል የሰው ኀይል ማፍራት ላይ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ በኮሚሽኑ እየለሙ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊም ኾነ አሉታዊ ተጽዕኖ ባላቸው ተቋማት ላይ እንዲተገበሩ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አንዱ በመኾኑ ተቋሙን ለማዘመን ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዘውዱ እምሩ (ዶ.ር) እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው እስከ አሁን ከ300 በላይ ስምምነቶችን ከውጭ ሀገራት እና ከሀገር ውስጥ ከሚገኙ ተቋማት ጋር ተፈራርሞ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ግማሽ የሚኾኑት ከሀገር ውስጥ ከሚገኙ ተቋማት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት መቻሉን አንስተዋል። አሁንም ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር የተደረገው ስምምነት ተግባራዊ እንዲኾን የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ዩኒቨርሲቲው እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል እና አገልግሎቶችን ጥራት ባለው መንገድ እና በአጭር ጊዜ ለመስጠት የፍትሕ ሥርዓቱን ሊያቀላጥፉ የሚችሉ መሠረተ ልማቶችን መዘርጋት ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

ከዚህ ውስጥ ደግሞ ተቋማቱን በአዳዲስ አሠራሮች ወይም በቴክኖሎጂ ማጠናከር አንዱ ተግባር መኾኑን ያነሱት አፈ ጉባኤዋ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን እንዲሁም የምርምር ተቋማት ቀዳሚውን ድርሻ ወስደው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከአዘዞ- አርበኞች አደባባይ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ አስታወቀ።
Next article“ዕድልና ፀጋን አሟጦ የተነተነ፣ ስጋቶችን የለየ እና ጥራት ያለው ዕቅድ ዝግጅት የራዕይ መዳረሻ ነው!” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር )