
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) እንደገለፁት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ 12 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ርዝመት ያለው ነው። የግንባታ ሥራው በራማ ኮንስትራክሽን ተቋራጭ ድርጅት ተይዞ የነበረ ቢኾንም ከኮንትራክተሩ የአቅም ማነስና ተያያዥ ችግሮች አንጻር ሥራው በሚፈለገው መጠንና ጊዜ ሳይፈጸም መቆየቱ አንስተዋል። በዚህ ምክንያትም የጎንደር ከተማ ሕዝብ የረጅም ጊዜ የመልካም አሥተዳደር ችግር ኾኖ መቆየቱን ኃላፊው አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሕዝቡን ጥያቄ በማዳመጥ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ አፈጻጸም ገምግመው በአዲስ መንገድ በተሻለ ተቋራጭ በፍጥነትና በጥራት እንዲፈጸም ማስቀመጣቸውንም አስታውሰዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔና አቅጣጫ መሰረትም የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በጎንደር የአስፋልት መንገዶች ጥገና ዲስትሪክት ተቋራጭነት ወደ ተሟላ የግንባታ ሥራ መግባቱንም ኃላፊው ገልጸዋል።
ከሚያዚያ ወር መጨረሻ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ፕሮጀክቱ የክልሉ መንግሥት፣ የከተማ አሥተዳደሩ እና ተቋራጩ የጋራ እቅድ በማውጣት ወደ ሥራ ከተገባ ጀምሮ በጣም ተስፋ ሰጭና አበረታች ተግባራት መፈጸማቸውን ገልጸዋል። ከማራኪ እስከ መሰረት ትምህርት ቤት 4 ኪ.ሜ መንገድ መገንባት የሚጠበቅ ሲኾን እስካሁን 1 ነጥብ 66 ኪ.ሜ መንገድ በአንደኛው የመንገድ አካፋይ የአስፋልት መንገድ ንጣፍ መሠራቱን ገልጸዋል ።
የመሃል አካፋይ ግንብ 340 ሜትር ርዝመት ያለው ኮንክሪት ግንባታ፣ የድጋፍ ግንብ 595 ሜትር ርዝመት የማሶነሪ ግንባታ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ መኾኑን ዶክተር ጋሻው ገልጸዋል። የመሃል አካፋይ ግንብ 2 ነጥብ 2 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው የግንባታ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
የመንገድ ዳርና ዳር የፓይፕ ግንባታና ዝርጋታ 441 ሜትር የሚሸፍን ሥራ እንደተሠራና በአማካኝ 17 ሜትር የሚረዝሙ መካከለኛ ድልድይ አንድ ያለቀ ሲኾን አንድ ተጨማሪ 50 በመቶ አፈጻጸም ላይ መኾኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይ ለአስፋልት ንጣፍና ለባዝኬርስ ሥራ የተዘጋጀ እስከ 3 ኪ.ሜ የሚሸፍን መንገድ እንደተዘጋጀ ነው ብለዋል ዶክተር ጋሻው። አብዘኛው የመንገድ ቆረጣ ሥራ በጥሩ ኹኔታ መሠራቱን ገልጸዋል ።
በቀጣይ ተጠናክረው የሚሠሩ የጠጠር ምርትና አቅርቦት፤ ቀሪ የስትራክቸር ግንባታ፤ የሙሊት ሥራ፤ የሲሚንቶና የአስፋልት ሬንጅ ግብዓት ማቅረብ ተግባራትን የሚመለከታቸው አካላት የጋራና ተናጠላዊ ድርሻን እንዲወጡ እንደሚደረግ አስረድተዋል ።
ፕሮጀክቱ የክልሉ መንግሥት በተቀመጠለት አቅጣጫ መሰረት ተፈጻሚ እንዲኾን ጥብቅ ክትትል እያደረገ መኾኑን ዶክተር ጋሻው ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!