በፀጥታ ችግር የቆሙ የልማት ጉድለቶችን የሚሞላ ሥራ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ገለጸ፡፡

27

ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን የ2017 በጀት ዓመት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በፍኖተሰላም ከተማ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ደኅንነት መምሪያ ኀላፊ አበባው አንተነህ የበጀት ዓመቱን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅድ አቅርበዋል።

ድህነትን መቀነስ፣ የሥራ ዕድልን ማበረታታት፣ የዋጋ ግሽበትን መቀነስ፣ የመንግሥት ገቢ እና ወጭን ማመጣጠን እንዲሁም ኢንቨስትመንትን መሳብ የበጀት ዓመቱ ዕቅድ ዋነኛ መለኪያ ሊኾኑ እንደሚገባ በዕቅዱ ተመላክቷል። በክልሉ ባለፈው ዓመት ባጋጠመው የፀጥታ ችግር የተዳከመውን የግብርና ዘርፍ ለማነቃቃት ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ነው የተገለጸው፡፡

ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ የ2017 በጀት ዓመት ዋና ሥራ ተደርጎ ርብርብ የሚደረግበት ስለመኾኑም ነው አቶ አበባው ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ ላይ የገለጹት። ዞኑ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ መሠብሠብ እና የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራትንም በስኬታማነት መፈፀም በበጀት ዓመቱ በትኩረት የሚሠሩ ግቦች ይኾናሉ ብለዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አባይ ዓለሙ፣ የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ አሥተዳደር መሪዎች በመድረኩ መሳተፋቸውን በብልጽግና ፓርቲ ከአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእንወድሃለን የሚሉትን ሕዝብ ማሸበር ለማን ይጠቅማል?
Next articleከአዘዞ- አርበኞች አደባባይ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ አስታወቀ።