አማራ ባንክ በ2016 በጀት ዓመት ከ377 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡

71

አዲስ አበባ: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ባንክ በዓመቱ ሥራ አፈጻጸም ከ377 ሚሊዮን በላይ ብር ትርፍ ማስመዝገቡን የባንኩ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጫንያለው ደምሴ አስታውቀዋል። ሥራ አስፈጻሚው በሰጡት መግለጫ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 25 ነጥብ 1 ቢሊዮን መድረሱን ጠቅሰዋል። የተሰበሰበውን ተቀማጭ ገንዘብ የፋይናንስ ተደራሽነትን ባማከለ አሠራር ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠቱንም ተናግረዋል።

ባንኩ በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ የቅርንጫፎችን ብዛት 311 ማድረሱን ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
በባንኩ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ለደንበኞች አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የባንኩ ሠራተኞችም ከ5 ሺህ በላይ መድረሱን አቶ ጫንያለው ገልጸዋል። በባንኩ ደንበኞች ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ የታገዘ የፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በማተኮር የዲጅታል ባንክ አገልግሎቶችን በተጠናከረ መልኩ ለማቅረብ ባንኩ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የሞባይል ባንኪንግ፣ የካርድ፣ የኤቲኤም እና የፖስ አገልግሎቶችን በማቅረብ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉም በመግለጫው ተመላክቷል።
አማራ ባንክ ከ571 ሺህ በላይ የሞባይል ተጠቃሚዎችንና ከ50 ሺህ በላይ ተገልጋዮችን ማፍራቱን በመግለጫው ተጠቅሷል።
ባንኩ በዓመቱ አፈጻጸሙ ስኬታማ እንዲኾን ድጋፍ ላደረጉ ባለ አክሲዮኖች ለቦርዱ አባላትና ለደንበኞች ምሥጋና አቅርበው በቀጣይ በበለጠ ተነሳሽነት ባንኩ ይሠራል ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደብረ ማርቆስ ከተማን በሚመለከት የሚሰራጨው መረጃ ሀሰት መኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ አስታወቀ፡፡
Next articleእንወድሃለን የሚሉትን ሕዝብ ማሸበር ለማን ይጠቅማል?