
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ምክንያት በአማራ ክልል የተወሰኑ ከተሞች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ሲታወኩ ይስተዋላል፡፡
ከምንም በላይ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ እስትንፋሳቸው በኾኑት ከተሞች የእንቅስቃሴ መዘጋት የሚፈጥረው ጉዳት ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ደብረ ማርቆስ ከተማ እንቅስቃሴ መታገዱን በሚመለከት መረጃዎች በስፋት እየተሰራጩ መኾኑ ይስተዋላል፡፡
አሚኮ ጉዳዩን በሚመለከት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴን በስልክ አነጋግሯቸዋል፡፡
ደብረ ማርቆስ ከተማ ከጠዋት ጀምሮ በመደበኛ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ናት ብለውናል፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያው የተሰራጨው መረጃ የከተማዋን ብሎም የክልሉን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ከመጉዳት በቀር የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም ነው ያሉት፡፡
የከተማዋን ፀጥታ ለማስጠበቅ የሚችል የፀጥታ ኀይል ስምሪት ወስዶ እየሠራ ነው ያሉት ከንቲባው የከተማዋ ነዋሪዎች በተረጋጋ ሁኔታ የእለት ከእለት የሥራ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያከናውኑ አሳስበዋል፡፡
መረጃን ከምንጩ ማጣራት እና የተለየ እንቅስቃሴ ቢኖር እንኳን ለፀጥታ ኀይሉ መረጃ መስጠት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
አሁን ያለው የኑሮ ውድነት እንኳን ሥራ አቁሞ እየተሠራ እንኳን ከበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች አቅም በላይ እየኾነ ነው ያሉት ከንቲባ መንበሩ በማኅበራዊ ሚዲያ የተሳሳተ እና ሕዝብን የሚጎዳ መረጃ ማሰራጨት ከሰብዓዊነት የወጣ ተግባር ነውም ብለዋል፡፡ ይህን መሰል የተሳሳተ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!