“በትምህርቱ ዘርፍ የገጠመንን ስብራት ለመጠገን በጋራ እና በትብብር መሥራት ይኖርብናል ” የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን

38

ደሴ፡ ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የተማሪ ምዝገባ የንቅናቄ መድረክ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የሕዝብ ተወካዮች በተገኙበት በደሴ ከተማ ተካሂዷል። የመድረኩ ተሳታፊዎች ባለፈው ዓመት በየወረዳቸው የተሻለ አፈፃፀም እንደነበር ገልፀው ለ2017 በጀት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል ።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በትምህርቱ ዘርፍ የገጠመንን ጊዜያዊና ስትራቴጂካዊ ስብራት ለመሻገር ችግሩን በመለየት፣ ከሚመለከተው አካል ጋር በመግባባትና በማሳተፍ ሥራዎችን በቁርጠኝነት ማከናወን ይገባል ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ አለምነው አበራ የ2017 የተማሪ ምዝገባ ዕቅድን ለማሳካት እንደየትምህርት ቤቶች የተማሪ ቁጥር ከ4 እስከ 7 አባላት ያሉት የትምህርት ኮማንድ ፖስት በማቋቋም ሥራዎች በቅንጅት ይሠራሉ ብለዋል፡፡

ኀላፊው አክለውም ትምህርት ቤቶችን በበጀት በመደገፍ፣ ተገቢውን ኦዲት ማስደረግ፣ የክረምት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠልና የተማሪ ምገባ እንዲጀመር የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ነው ያሉት፡፡
በመድረኩ በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ወረዳዎች እውቅናና ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።

ዘጋቢ ፦አንተነህ ፀጋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፈተናውን በጽናት እና በማስተዋል የሚሻገር መሪ፤ ሀገርንም ሕዝብንም ማሻገር ይችላል” አቶ ደሳለኝ ጣሰው
Next articleየደብረ ማርቆስ ከተማን በሚመለከት የሚሰራጨው መረጃ ሀሰት መኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ አስታወቀ፡፡